አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙስናን ለመከላከል የሚያስችሉ ተጠያቂነት ያለው አሰራር መዘርጋት እንዳለባቸው ተጠቆመ

269

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለሙስናና ብልሹ አሰራር የሚዳርጉ አሰራሮችን በማስተካከል ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ማስፈን እንዳለባቸው ተጠቆመ።

መንግሥት ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ ተቋማት አሰራራቸውን ለማዘመንና የሙስና ትግላቸውን ለማጠናከር ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም ተመላክቷል።

በሙስና ወንጀልና ሕገ-ወጥ ድለላ ዙሪያ በሚፈጠሩ ሁለንተናዊ ችግሮች ዙሪያ የሚዳስሱ ጥናቶች በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተከናውነዋል።

በጥናቶቹ ላይ የሚመክር የሁለት ቀናት አውደ-ጥናትም በዩኒቨርሲቲው ዛሬ ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ፤ ዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጣቸው ተልዕኮዎች መካከል የማኅበረሰብ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን ማከናወን አንዱና ዋነኛው ኃላፊነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ መሰረትም የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ለሕዝቡ አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ተቋማት ላይ የሚስተዋለውን ሙስና እና ብልሹ አሰራር በተመለከተ ጥናት ማድረጉን ተናግረዋል።

በጥናቱ ሙስና በሀገርና በሕዝቡ ሃብት ላይ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ በማመላከት የመፍትሄ ሃሳብ ጭምር አቅርቧል ብለዋል።

በመሆኑም በአገር ህልውና ላይ አደጋ የደቀነውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የምሁራን መፍትሔ ተኮር ጥናት ወሳኝ መሆኑን ዶክተር ተመስገን ገልጸዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

የሙስና እና ብልሹ አሰራር ችግሮችን በማመላከት የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ የተደረገው ጥናትም ጥሩ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አለማየሁ ደበበ፤ "ንቅዘት እና ሙስና" በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ማህበራዊና የኢኮኖሚ መስኮች ከባድ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ከ100 በላይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ዩኒቨርሲቲው በሰራቸው 21 የጥናት ውጤቶች ችግሩን በማሳየት መፍትሔም ለማመላከት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

በጥናቱ ሙስና እና ሕገ-ወጥ ድለላን ለመከላከል የሚያስችሉ ምክረ-ሃሳቦች መቅረባቸውም ተገልጿል።

በመሆኑም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለሙስና እና ብልሹ አሰራር የሚዳርጉ አሰራሮችን በማስተካከል ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ማስፈን እንዳለባቸው ተመላክቷል ነው ያሉት።

በተለያዩ ተቋማት ላይ የሚስተዋለውን የሙስና እና ብልሹ አሰራር ችግር በተመለከተ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው ጥናት ከ60 በላይ ምሁራን መሳተፋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም