የአምራች ኢንተርፕራይዝ ልማትን ለመምራት የሚያስችል የአሥር ዓመት ፍኖተ-ካርታ እየተዘጋጀ ነው

290

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 23/2015 የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዝ ልማትን በውጤታማነት ለመምራት የሚያስችል የአሥር ዓመት ፍኖተ-ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ገለጸ።

በአሥር ዓመቱ ፍኖተ-ካርታ ዙሪያ ከአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ማኅበራት ተወካዮች፣ የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ሞዴል ኢንተርፕራይዞች ጋር ውይይት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጳውሎስ በርጋ፤ ጠንካራ ተቋም ለመገንባት የአሥር ዓመት ፍኖተ-ካርታ መዘጋጀቱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ፍኖተ-ካርታው ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚደረጉ ድጋፎችን ለማጠናከርና የሚሰሯቸውን ሥራዎችም ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በተጓዳኝም የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማስፋትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ምቹ መደላድሎችን እንደሚፈጥርም ነው የጠቆሙት።

የፍኖተ-ካርታው ዝግጅት ቡድን መሪ ሰለሞን ወሌ በበኩላቸው፤ ፍኖተ-ካርታው የተቋሙን ስትራቴጂ በአግባቡ ለመተግበር በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም የባለድርሻ አካላት አስተያየት ለፍኖተ-ካርታው በግብዓትነት እንደሚካተት ጠቁመዋል።

በአገሪቱ የሚገኙ ከ48 ሺህ በላይ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በሚሊየን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም