በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ለሚካሄደው ሕዝበ-ውሳኔ ስኬታማነት በቂ ዝግጅት ተደርጓል- ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ

206

አዲስ አበባ ጥር 23/2015 (ኢዜአ)፦በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሚካሄደውን ሕዝበ-ውሳኔ በተሳካ መልኩ ለማከናወን በቂ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሥር የሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሕዝበ-ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ለማከናወን በሂደት ላይ ይገኛል።

ለሕዝበ-ውሳኔው የመራጮች ምዝገባ የተጠናቀቀ ሲሆን 3 ሚሊዮን ዜጎች ድምፅ ለመስጠት መመዝገባቸውም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ተቋሙ ባለፉት የአደረጃጀት ሕዝበ- ውሳኔና የብሔራዊ ምርጫ ሂደቶች የተሻለ ልምድ ማግኘቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም በክልሉ ሥር የሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ለሚካሄደው ሕዝበ-ውሳኔ ስኬታማ ክንውን በቦርዱ በኩል በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በምርጫ ሂደት የሚያጋጥሙ ጉድለቶች የሚሻሻሉበት እና አፋጣኝ እርማት የሚወሰድበት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።

በሕዝበ-ውሳኔው በነበረው የመቀጠል ወይም በአዲስ መደራጀት በሚሉት ሁለት የተለያዩ አማራጮች ክርክርና ውይይት እንዲያደርጉና የተሻለ የምርጫ ልምምድ እንዲኖር ተሰርቷል ብለዋል።

በሂደቱም መራጮችን በፆታ፣ በዕድሜ እና የአካል ጉዳት ካለ በማረጋገጥ የተጣራ መረጃ በማደራጀት የመራጮች ምዝገባ ተከናውኖ ተጠናቋል ነው ያሉት።

በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችም በመራጭነት እንዲሳተፉ ለማድረግ ምዝገባ መካሄዱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ እና ሌሎች የሲቪል ማህበራት በምርጫ ሂደቱ መራጮች እንዲሳተፉ በማስተማር እና አፈጻጸሙን እንዲከታተሉ ፈቃድ መሰጠቱንም ተናግረዋል።

ለምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በ31 ማዕከላት እንዲደርሱ የማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም ሕዝበ-ውሳኔውን ለማካሄድ በቂ ዝግጅት መደረጉንና የድምፅ አሰጣጡን ለማከናወን የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

በምዝገባ ሂደቱ ላይ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ በወንጀል ጭምር የሚያስጠይቁ የሕግ ጥሰቶች ተፈጽመው በመገኘታቸው የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።

ቦርዱ የምርጫ አፈጻጸም ሂደቱን በተሻለ እውቀት፣ ልምድና አቅም የክትትል ቡድን በማዋቀሩ በችግሮች ላይ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰዋል።

በእርምጃው ምዝገባው እንዲሰረዝ መደረጉን ገልጸው፤ የሕግ ጥሰቱን የፈጸሙ ግለሰቦችም በወንጀል ጭምር እንዲጠየቁ ከፌደራል ፖሊስ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ቦርዱ ተዓማኒነቱን በመጨመር የዜጎችን የመራጭነት መብት እንዲረጋገጥ በግልጸኝነትና እውነተኝነት መርህ ላይ ተመስርቶ የሚፈጠሩ ስህተቶች አፋጣኝ የተጠያቂነት ምላሽ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑንም ዋና ሰብሳቢዋ አረጋግጠዋል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ደራሼ) ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም የሕዝበ- ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ የሚከናወን መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም