በሀገራዊና ከተማዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ውይይት በአዲስ አበባ ከተማ ተካሄደ

121

አዲስ አበባ ጥር 23/2015 (ኢዜአ) በሀገራዊና ከተማዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ውይይት በአዲስ አበባ ከተማ ተካሄደ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እና ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመሩት ስብሰባ አዲስ አበባ ከተማ ከለውጡ ወዲህ ባሳካቻቸው ስራዎች፣ ፋዳዎቻቸውና ተግዳሮቶች እንዲሁም መፍትሔዎቻቸውን መሰረት አድርጎ አሁን እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች እንዴት መሻገር እንደሚገባ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተካሂዷል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ በርካታ ታላቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የከተማዋን ገጽታ መቀየር ከመቻሏም በላይ በሰው ተኮር የልማት ስራዎች የህዝቡን ችግሮች ማቅለል ያስቻሉ ውጤቶች መመዝገባቸውን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ታላላቅ ስኬቶች ዕውን መሆን የቻሉት በፈተና ውስጥም ቢሆን በጥበብና በላቀ ትጋት ሕዝቡን በማሳተፍ መምራት በመቻሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የስብሰባው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከተማዋ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች አመራሩ በእምነትና በዕውቀት ስራውን መምራት በመቻሉ መሆኑን ጠቅሰው ከስኬቶች በመማር ለቀጣይ የላቀ ስራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ አብዛኛው አመራር ተልእኮውን በብቃት ለመወጣት ጥረት እያደረገ ቢሆንም አንዳንድ አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች በመሬት ወረራ እና በሌሎች የሌብነት ስራዎች ውስጥ የሚሳተፈፉ መሆኑን አንስተው የተጀመረው የጸረ ሌብነት ትግል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና የህግ የበላይነት የማስከበር ስራ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ሕዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ መንግስትና ህዝብ እንዳይተማመኑ ጥርጣሬ የሚያነግሱ ሀሰተኛ ትርክቶችንና አሉባልታዎችን በመለጠፍ ላይ የሚገኙ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ መንግስት እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ተሰብሳቢዎቹ አሳስበዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የተጀመረው የጸረ ሌብነት ትግል፣መንግስታዊ አገልግሎቶች ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው በነጻ ሚዲያ ስም በሕዝቦች መካከል አለመተማመንን ለማንገስ ሀሰተኛ ወሬዎችን በሚዲያ በሚያናፍሱት ላይ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አቶ አዳም ፋራህ በበኩላቸው ጽንፈኝነት በሀይማኖትም ይሁን በብሔር መልክ የሚገለጽ ሲሆን ጥርጣሬንና አለመግባባትን የሚያነግስ በመሆኑ ለብልጽግናችን ጠንቅ በመሆኑ አስተሳሰቡንና ድርጊቱን መታገል ይገባል ብለዋል፡፡

ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በከተማው የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች መስራትና የኢኮኖሚ ተዋንያኑ ሚናቸውን ባግባቡ እንዲወጡ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው መግለፃቸው ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም