በዓሉን በማልማትና በማሳደግ ለኢኮኖሚና ሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚነት ማዋል ይገባል---ዶክተር ይልቃል ከፋለ

146

እንጅባራ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 የአገው ፈረሰኞች በዓልን በማልማትና በማሳደግ ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ለማዋል በትኩረት መስራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ።

የአገው ፈረሰኞች ማህበር 83ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ፌስቲቫል በፈረስ ትርኢቶች፣ባህላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜዎች ታጅቦ በእንጅባራ ከተማ በድምቀት ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበዓሉ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል ታሪክን ከማስታወስ ባለፈ ለክልሉም ሆነ ለአገር ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው።

የጀግኖች አባቶችን ተጋድሎና የፈረስ ውለታን የሚዘክር በዓል በመሆኑ እውቀትና ጥበብን ተጠቅሞ በዓሉን ከማዳበር ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት አስተዋጾ እንዲኖረው በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ባህልን ለይቶ ማጥናትና ማስፋት እንደሚገባ ያመለከቱት ዶክተር ይልቃል፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል በህዝቡ ላይ መንፈሳዊ እርካታ ለመፍጠርና ለበለጠ ሥራ እንዲነሳሳ ለማድረግም ይረዳል ብለዋል።

የበዓሉን ተሳታፊዎች ቁጥር በማሳደግ በዓሉ በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ ከማድረግ ባለፈ ለኢኮኖሚ ምንጭና ለሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽኦ እንዲኖረው በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል

የአገው ፈረሰኞች በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በሚደረግ ጥረት ሁሉ የክልሉ መንግስት የበኩሉን እንደሚወጣ አስረድተዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኘው በበኩላቸው፣ በዓለም ላይ ለአገራቸው ነጻነት ለተዋደቁና በሌሎች መስኮች ፋና ወጊ ተግባር ለፈጸሙ ግለሰቦች ሃውልት ማቆም የተለመደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአገው ህዝብም በጣልያን ወረራ ወቅት ጀግኖች አባቶች ያደረጉትን ተጋድሎና ፈረስ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በአገው ፈረሰኞች ማህበር አማካኝነት በየዓመቱ በመዘከር ለትውልድ ህያው ሃውልት እያቆመ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዓሉን በማልማት፣ በመጠበቅና በመንከባከብ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ከብሔሩ ተወላጆች በተጨማሪ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አስተላልፈዋል።

"በአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል በየዓመቱ የሚካሄደው ፌስቲቫል ለእንጅባራ ከተማ አስተዳደር እድገት አስተዋጽኦ እያደረገ ነው" ያሉት ደግሞ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ግዛቸው አጠና ናቸው።

አካባቢው በማዕድን ሃብት፣ በእንስሳት፣ በሰብል፣ በእጽዋት፣ በመድሃኒት ቅመማና ባህል ጥናት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች እምቅ ሃብትና ጸጋ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በከተማዋ በመረጡት ዘርፍ ለመሰማራት ቢመጡ በአስተዳደሩ በኩል ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።

በከተማው በአገው ፈረሰኞች ፌስቲቫል ላይ የተመሰረተውን የቱሪዝም ልማት በሌሎች የኢኮኖሚ አማራጮች ለመደገፍ የባለሀብቶች አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም