በጀጎል ግንብ ዙሪያ የተጀመረው ህገ-ወጥ ግንባታን የመከላከል ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

125

ሀረር (ኢዜአ) ጥር 23/2015 በጀጎል ግንብ ዙሪያ የተጀመረው የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ- መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡

የሀረሪ ብሄራዊ ጉባኤ 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል፡፡

ጉባኤው በቆይታው የብሄራዊ ጉባዔውን 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ቃለ-ጉባኤ አድምጦ ያጸደቀ ሲሆን፤ የክልሉን የባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የክልሉን ትምህርት ቢሮ የ6 ወራት የስራ አፈፃፀምን ገምግሞ አፅድቋል፡፡

የሀረሪ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በጉባዔው ላይ እንዳሉት የሀረሪ ዕደ-ጥበብ ውጤት የሆነው የሀረሪ አለላ ስፌት በዓለም የንግድ ምልክትነት መመዝገቡ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

በሌላ በኩል የጀጎል ግንብ ዙሪያውን ከፍተኛ የሆነ ህገ-ወጥ ወረራ ያጋጠመው እንደነበር በማስታወስ ቅርሱን ከአደጋ ለመታግ በተሰራው ስራ በተለይም ህገ-ወጥ ግንባታ ላይ በተወሰደው እርምጃ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በቅርሱ ዙሪያ የተገነቡ ህገ-ወጥ ግንባታዎችን በማስወገድ ቅርሱን በዘላቂነት ለመንከባከብ ይሰራል ነው ያሉት።

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘውም የጀጎል ውስጣዊ ክፍልን ለነዋሪው ምቹ ለማድረግ የፍሳሽ አወጋገድ ጋር በተገናኘ ያጋጠሙ ቸግሮችን ለመፍታትም በትኩረት ይሰራል፡፡

በሌላ በኩል የሀረሪ ቋንቋን ለማሳደግና የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ያሉ ሲሆን ወላጆችም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡

የሀረሪ ጉባኤ አባል የሆኑት ወይዘሮ ፈሪሃ መሃመድ በበኩላቸው በጀጎል ግንብ ዙሪያ ቅርሱን ከአደጋ ለመታደግ የተወሰዱ እርምጃዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልፀው የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ ያሉ ሌሎች ቅርሶችም አስፈላጊው ጥገና እና እድሳት ሊደረግለቸው እንደሚገባም በማውሳት።

በክልሉ ዘንድሮ በትምህርት ሴክተሩ በተለይም በ12ኛ ክፍል የተገኘው ውጤት የተሻለ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ሌላኛዋ የሀረሪ ብሄራዊ ጉባኤ አባል ወይዘሮ ነቢላ ማህዲ ናቸው፡፡

በክልሉ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 44 በመቶዎቹ ማለፋቸውን ገልጸው፤ የትምህርት ቤት ግንባታና ማስፋፊያዎችን ተግባራዊ ከማድረግ ጎን ለጎን በቀጣይ ፈተናውን የሚወስዱ ተማሪዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ በማንሳት።

ጉባኤው በአፈ-ጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድ የቀረበለትን የወይዘሮ ፎዚያ በክሪን የጉባኤው ፅህፈት ቤት ሃላፊነት ሹመት ተቀብሎ በማጽደቅ ሁባኤውን አጠናቋል፡፡

የሀረሪ ብሔራዊ ጉባኤ የሀረሪ ብሔረሰብ ቋንቋና ባህልን በሚመለከት ፖሊሲና ህግ የሚያወጣ፤ በቅርስ አጠባበቅ ዙሪያም መመሪያ የሚያወጣ ሆኖ 14 መቀመጫዎች አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም