የጤና መድህን አገልግሎት በሁሉም የአርብቶ አደር አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው

106

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 በአገሪቱ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የጤና መድህን ሥርዓት በሁሉም የአርብቶ አደር አካባቢዎች ለማስፋት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ።

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነች ካለው ለውጥ ውስጥ ፍትሃዊ፣ አቅምን ያገናዘበ፣ አካታችና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ አንዱ ነው።

አካታችና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ በኩል ካለፉት አሥር ዓመታት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የጤና መድህን ሥርዓት ተጠቃሽ ነው።

አገልግሎቱን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በ894 ወረዳዎች ተግባራዊ በማድረግ ከ45 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

በዚህም በከፍተኛ የሕክምና ወጪ ምክንያት በሕብረተሰቡ ላይ ይደርስ የነበረውን የጤናና ምጣኔ ኃብት ቀውስ መቀነስ ተችሏል።

የአፋር፣ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልል የጤና ኃላፊዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጤና መድህን ሥርዓት አርብቶ አደሩ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ የጤና አገልግሎትን በቀላሉ እንዲያገኝ አስችሏል።

በዚህም ለዜጎች ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ላሉ ተግባራት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን ሃቢብ እንደተናገሩት፤ አገልግሎቱ በክልሉ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ሕብረተሰቡ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ይቸገር እንደነበር አስታውሰዋል።

የጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ግን በዓመት አንድ ጊዜ በሚያዋጡት ወጪ በቀላሉ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረጉ ለአርብቶ አደሩ እፎይታን ፈጥሯል ብለዋል።

በሶማሌ ክልል የጅግጅጋ ቅርንጫፍ የጤና መድህን ሥራ አስኪያጅ አብዱልናስር አህመድ ኑር በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ በገንዘብ ምክንያት ያጋጥም የነበረውን የጤና አገልግሎት እጥረት መቅረፉን ገልጸዋል።

በአሮሚያ ክልል የምስራቅ ሐረርጌ ጤና መምሪያ ኃላፊ መሐመዲን ክብረወሰን አገልግሎቱን በሁሉም ወረዳዎች ማዳረሳቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ ጥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የአገልግሎት ጥራቱን በማሻሻል በሁሉም የአርብቶ አደር ወረዳዎች ለማድረስ እየሰሩ መሆኑን ኃላፊዎች ገልጸዋል።

የጤና መድህን አገልግሎት አባላት ቅድሚያ በሚያዋጡት አነስተኛ መዋጮ ከነቤተሰቦቻቸው የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት ነው።

በኢትዮጵያ ባለፉት አሥር ዓመታት ተግባራዊ መደረጉ የጤና እክል ሲያጋጥም ፈጣን የሕክምና አገልግሎት ለማግኘትና ለጤና በሚወጣ ወጪ ምክንያት ዜጎች ለከፍተኛ ድህነት እንዳይዳረጉ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት 11 በመቶ የሚሆኑት ዜጎች የጤና ወጪያቸውን መሸፈን ባለመቻላቸው ምክንያት የጤና ችግር ቢያጋጥማቸውም ወደ ጤና ተቋም አይሄዱም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም