የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት በፍትህ አሰጣጥ ዙሪያ ከዳኞች ጋር ተወያዩ

198

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አበባ እምቢአለ በዳኝነት ስርዓቱ ዙሪያ በሚታዩ ችግሮችና ሊወሰዱ በሚገባቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ከዳኞች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥን የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦም ውይይት የተደረገ ሲሆን ከሶስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተውጣጡ 150 ዳኞች መሳተፋቸውም ተገልጿል።

ከዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች ላይ መፍትሔ ማበጀት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሆነም ተጠቁሟል።

ዳኞችና አመራሮች አንድ ሆነዉ በትብብር የመስራት አስፈላጊነት፣ ከሕዝብ የሚነሱ ቅሬታዎች በፍጥነት ምላሽ የሚያገኙበትና የዳኞችን ፍላጎት ባማከለ መንገድ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የሚሰጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም እንደሚረዳ ተመላክቷል።

በተጨማሪም የዳኞች የስነ-ምግባር እንዲሁም ለዳኝነት ስራው አጋዥ የሆኑ የግብአት አቅርቦቶች ጉዳዮችም ውይይት የተደረገባቸው አጀንዳዎች መሆናቸውም ተጠቁሟል።

ከዳኞች ጋር የተደረገው ውይይት በቀጣይ ለሚከናወኑ ስራዎች እንደ ግብዓት እንደሚያገለግልም ተጠቅሷል።

በቀጣይም ከአስተዳደር ሰራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተመሳሳይ የውይይት መድረኮች እንደሚኖር ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም