በወላይታ ዞን ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባ የበዴሳ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ተመረቀ

178

ሶዶ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 በወላይታ ዞን ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባ የበዴሳ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ተመርቆ መከፈቱ ተገለጸ።

ኮሌጁን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድርና የክልሉ ከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ ናቸው።

የደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር እንዳልካቸው ጌታቸው በምረቃ ስነ- ስርአቱ ላይ እንዳሉት በክልሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆነው የቆዩ 13 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ግንባታን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት ተችሏል።

ከተጠናቀቁት መካከል የበዴሳ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ለግንባታው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።

ኮልጁ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ330 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ለማስልጠን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን ጠቁመዋል።

በዘርፉ ብቃት ያለውና በክህሎት የዳበረ እንዲሁም ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ሀይል በብዛት ለማፍራት ያለው አበርክቶ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

በክልሉ የሚገኙ ኮሌጆችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር ዘርፉን ለማሳለጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የሰልጣኞችን የብቃት ምጣኔ በማሻሻል ረገድ ኮሌጆች የሚሰጡትን ስልጠና እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ከማስፋፋት አንፃር አበክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው የበዴሳ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ግንባታ ላለፉት ሰባት ዓመታት መጓተቱን አስታውሰዋል።

በህንፃ ተቋራጮች ድክመት ግንባታው መስተጓጎሉን ጠቅሰው ይህንኑ ተከትሎ በተወሰደ እርመጃ ውል ተቋርጦ ለሌላ የህንፃ ተቋራጭ በቁርጥ ዋጋ በመሰጠቱ ግንባታው በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ መደረጉን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ብቁ ተወዳዳሪና ስራ ፈጣሪ ዜጋ ማፍራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ በቀጣይ ይህንን ተሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ አውስተዋል።

ዘርፉ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ድጋፋቸውን እንዲያጎለብቱ ጠይቀዋል።

በኮሌጁ ምረቃ ስነ-ስርአት ላይ ከክልል፣ ከዞንና ከከተማዋ የተውጣጡ የስራ ሀላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም