ኢትዮጵያ እና ተርኪዬ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠት እና በወንጀል ጉዳዮች ላይ የጋራ የሕግ ትብብር ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ተወያዩ

145

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 ኢትዮጵያ እና ተርኪዬ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠት እና በወንጀል ጉዳዮች ላይ የጋራ የሕግ ትብብር ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ተወያዩ፡፡

በጉዳዩ ላይ የጋራ ውይይት ለማድረግ በተርኪዬ ሪፐብሊክ መንግስት ምክትል የፍትሕ ሚኒስትር የሚመራ የልዑካን ቡድን በኢትዯጵያ የስራ ጉብኝት አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ እና በተርኪዬ መንግስታት መካከል ያለው የሕግና ፍትሕ የሁለትዮሽ ትብብር በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት በተርኪዬ ሪፐብሊክ መንግስት ምክትል የፍትሕ ሚኒስትር ሚስተር ያኩፕ ሞጉል የሚመራ ልዑክ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ማድረጉን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ  ከፍትሕ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና ከመንግስት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደው ጋር መወያየታቸውም ተገልጿል፡፡

ሁለቱ ሀገራት እ.ኤ.አ. ግንቦት 10/2022 በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ማድረግ የሚያስችል የስምምነት ሰነዶች መፈራረማቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ስምምንቶቹን ሀገራቱ ስልጣኑ ባላቸው አካላት አማካኝነት ፀድቀው ተግባራዊ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውም ተጠቁሟል።

በምክክር መድረኩ በአቅም ግንባታ እና በፎረንሲክ ምርመራ ዙሪያ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረሙት መግባቢያ ሰነዶች ተግባራዊ እንዲሆኑ መከናዎን ስለሚገባቸው ስራዎች እንዲሁም በሌሎች ሕግ እና ፍትህ ነክ አጀንዳዎች ላይም ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል።

በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ አባላት የአንድነት ፓርክ እና የፍትሕ ሚኒስቴር ዋናው መስሪያ ቤትን ጉብኝተዋል።

በተርኪዬ ምክትል የፍትሕ ሚኒስትሩ የተመራው የልዑካን ቡድን አባላትም ሚስተር ቃሲም ሲሴክ፣ ሚስተር ሙስታፋ ጣይፕ ሲሴክ፣ ሚስተር መህመት ሳሊህ እና ሚስተር መህመት ኤሪገን ሲሆኑ በኢትዮጵያ የተርኪዬ አምባሳደር እና ምክትላቸውም መሳተፋቸውን የሚንስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም