ሙስና እና ብልሹ አሰራር በሀገሪቱ ላይ እያሳደሩ ያሉትን ተፅእኖ ለመከላከል የምርምር ስራዎችን አጠናክረን መስራት ይኖርብናል-ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ

207

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 23/2015 ሙስና እና ብልሹ አሰራር በሀገሪቱ ላይ እያሳደሩ ያሉትን ተፅእኖ ለመከላከል የምርምር ስራዎችን አጠናክረን መስራት ይኖርብናል ሲሉ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ተናገሩ።

በዛሬው እለት በሀገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ባሉ የድለላ ተግባራት ላይ በተሰሩ የምርምር ስራዎች በሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ አውደ ጥናት እየተካሄደ ይገኛል።

አውደ ጥናቱ “ሴክተር ተኮር የሙስና ሁኔታ ዳሰሳ እና የደላሎች ሚና የምርምር ውጤቶች” በሚል መሪ ሀሳብ  እየተካሄደ ያለው፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የዩንቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች እና ሌሎች ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የዩንቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አለማየሁ ደበበ በአውደ ጥናቱ ላይ እንደገለፁት ንቅዘት እና ሙስና በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በሰዎች ስነ-ልቦና ላይ የሚያሳድሩት ተፅእኖ ቀላል አይደለም ብለዋል።

ይህንንም ለመቅረፍ ዩንቨርሲቲው ያጠናቸው 21 የምርምር ውጤቶች በመድረኩ ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል ብለዋል።

በዚህም መሰረት በድለላ ተግባራት ላይ አተኩረው የተሰሩ አስር ጥናቶች፣ በንቅዘት ላይ የሚያጠነጥኑ ዘጠኝ ጥናቶች እንዲሁም ሁለት የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰሩ የምርምር ስራዎች በአውደ ጥናቱ እንደሚቀርቡም ገልፀዋል።

አያይዘውም የምርምር ስራዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን የሚያስገኙ መሆኑን ጠቁመው ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ለመንግስት የፖሊሲ ምክረ-ሃሳብ ለማቅረብ ያግዛል።

አወደ-ጥናቱ ዛሬን ጨምሮ እስከ ነገ እንደሚቆይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም