በቻን ውድድር ለፍጻሜ የሚያልፉ አገራት ዛሬ ይለያሉ

104


አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 23/2015 በሰባተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) አስተናጋጇ አገር አልጄሪያ ከኒጀር፤ ማዳጋስካር ከሴኔጋል ዛሬ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።


19ኛ ቀኑን ያስቆጠረው የቻን ውድድር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።


ወደ ፍጻሜ የሚያልፉ አገራት የሚለዩበት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።


ከምሽቱ 1 ሰአት በሚሉድ ሀዴፊ ስታዲየም አስተናጋጇ አገር አልጄሪያ ከኒጀር ይጫወታሉ።

አልጄሪያ ኮትዲቭዋርን እንዲሁም ኒጀር ጋናን በሩብ ፍጻሜ በማሸነፍ ነው ለግማሽ ፍጻሜው ያለፉት።


በሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በውድድሩ የመጀመሪያ ተሳትፎዋ ስኬታማ ጉዞ እያደረገች የምትገኘው ማዳጋስካር ከሴኔጋል ጋር ከምሽቱ 4 ሰአት በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ጨዋታዋን ታደርጋለች።


ማዳጋስካር በሩብ ፍጻሜው ሞዛምቢክን እንዲሁም ሴኔጋል ሞሪታኒያን ማሸነፋቸው ይታወቃል።


የግማሽ ፍጻሜ አሸናፊ አገራት የፊታችን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም የፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።


የቻን ውድድር በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም