ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በማሸነፍ ጉዞው ቀጥሏል

501

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 22/2015 በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሊጉ ስድስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዘገበ።


በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቻልም ድል ቀንቶታል።


የፕሪሚየር ሊጉ የስድስተኛ ሳምንት መርሐግግብ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በድሬዳዋ ከተማ ተካሄደዋል።


የሊጉ መሪ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፋሲል ከነማን 37 ለ 20 አሸንፏል።


ውጤቱንም ተከትሎ ቂርቆስ ነጥቡን ወደ 12 ከፍ ያደረገ ሲሆን እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ እስከ አሁን ያደረጋቸውን ስድስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ በአስደናቂ ግስጋሴው ቀጥሏል።


በሌላ ጨዋታ መቻል ኦሜድላን 37 ለ 31 አሸንፏል። ነጥቡንም ወደ 10 ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪ ይከተላል።


ትናንት በተደረጉ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባህር ዳር ከነማ ሚዛን አማን ከተማን 35 ለ 25 ሲያሸንፍ ፌደራል ማረሚያ እና ከምባታ ዱራሜ 22 አቻ ተለያይተዋል።


የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ከአምስተኛ እስከ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች በድሬዳዋ ከተማ እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ማሳወቁ ይታወቃል።


በዚሁ መሰረት ውድድሩ እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም