ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ከ217 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል

95

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 22/2015 በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በኢንተርፕራይዞች የአገር ውስጥ ምርት በመተካት ከ217 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ።

ለኢንተርፕራይዞች ስራ ማስኬጃ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ማቅረብ መቻሉን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ፤ የተቋማቸውን የስድስት ወራት አፈጻጸም በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ለኢንተርፕራይዞች ከ5 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት የመስሪያና መሸጫ ቦታ መሰጠቱን አቶ አብዱልፈታ ገልጸዋል።

ለሥራ ማስኬጃና ለሊዝ ማሽን ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።

1 ሺህ 750 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለማቋቋም ታቅዶ 2 ሺህ 196 በማቋቋም ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን አመልክተዋል።

አዳዲሶችን በማቋቋምና ነባር ኢንተርፕራይዞችን በማጠናከር ጭምር በተከናወኑ ስራዎች ከ47 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩንም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

ኢንተርፕራይዞችን የኤክስፖርት አቅምን ማሳደግ መቻሉንና ከዘርፉ ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በኢንተርፕራይዞች የአገር ውስጥ ምርት በመተካት ከ217 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉንም አክለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 217 አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ እንዲሁም 48 መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ደግሞ ወደ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዝነት መሸጋገራቸው በመግለጫው ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም