ማህበረሰቡ በስጋ ደዌ በሽታ ላይ ያለውን አመለካከት ለመቅረፍ የግንዛቤ መፍጠር ተግባር ልዩ ትኩረት የሚያሻው ነው - የበሽታው ተጠቂዎች

289

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 22/2015 "ማህበረሰቡ በስጋ ደዌ በሽታ ላይ ያለውን አመለካከት ለመቅረፍ የግንዛቤ መፍጠር ተግባር ልዩ ትኩረት ሊሰራበት ይገባል" ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የበሽታው ተጠቂዎች ገለጹ።

ዓለም አቀፍ የሥጋ ደዌ ቀን በኢትዮጵያ ለ24ኛ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ69ኛ ጊዜ ''የሥጋ ደዌ በሽታን አንዘንጋው!'' በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።

የስጋ ደዌ ማይክሮ ባክቴሪየም ‘ሊፕሬ' በተስኘ ባክቴሬያ የሚመጣ ሲሆን በወቅቱ የሕክምና እገዛ ካልተደረገ በአካልና ሥነ-ልቦና ላይ ጉዳት የሚያደርስ በሽታ ነው።

ይህ በሽታ በኢትዮጵያ "በእርግማንና በዘር የሚተላለፍ" ተደርጎ በተሳሳተ መንገድ የሚታሰብ በመሆኑ ተጠቂዎች ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲጋለጡ ቆይተዋል።

የስጋ ደዌ ተጠቂ የሆኑት አቶ አሰበ ዘውዴና አቶ አያሌው ተፈራ እንደሚሉት፤ በኅብረተሰቡ ለሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ያለው የተሳሳተ አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች አሳይቷል።

ይሁን እንጂ አሁንም ትክክለኛውን ግንዛቤ በመጨበጥ ረገድ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስፋት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል የበሽታው ተጠቂ የማህበረሰብ ክፍሎች ፍትሃዊ ተጠቀሚነታቸውን ለማረጋገጥና በተለይም ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የበሽታው ተጠቂዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ሴቶች ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሃና የሺንጉስ እንዳሉት፤ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች የሚደርስባቸውን ማኅበራዊ መገለልና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ለማሻሻል "የተለያዩ ተግባራት "እየተከናወኑ ነው።

ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ አበረታች ለውጦች ቢመዘገቡም የበሽታው ተጠቂዎች ከአድሎና መድሎ ነጻ በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ አሁንም ብዙ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

መንግስት ከስጋ ደዌ በሽታ የጸዳ ትውልድ ለመፍጥርና የበሽታው ተጠቂዎች ፍትሃዊ ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግሥት ከባለደርሻ አካላት ጋር የሚሰራውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማኅበር ሊቀ-መንበር አቶ ከፍያለው በቀለ በበኩላቸው በሽታው ከሚያስከትለው አካል ጉዳተኝነት ነጻ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የበሽታው ተጠቂ የማህበረሰብ ክፍሎችም በተለያዩ ዘርፎች ያሏቸውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ማህበሩ ሕብረተሰቡ ስለ በሽታው ያለውን ግንዛቤ ለማጎልበትና የበሽታው ተጠቂዎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ20 ሺ በላይ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም