በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምናደርገውን ተሳትፎ አጠናክረን እንቀጥላለን - ዳያስፖራዎች

180

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 21/2015 በተለያዩ አገር የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናገሩ።

የዳያስፖራ አባላቱ ለገዳዲ በሚገኘው ድሬ ግድብ አካባቢ የተከሏቸውን ችግኞች የመንከባከብ ሥራ በዛሬው ዕለት አከናውነዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዳያስፖራ አባላት እንደገለጹት፤ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን በተከታታይነት የእንክብካቤ ሥራ መሥራት ይገባል።

ይህንንም ተከትሎ ከዚህ ቀደም የተከሏቸውን ችግኞች ከኢትዮጵያ የዳያስፖራ አገልግሎት ጋር በመተባበር እየተንከባከቡ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም የችግኞች የጽድቀት ደረጃ ለመከታተል የሚያስችል የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓት መዘርጋቱ የተከሏቸውን ችግኞቹን ለመንከባከብ እድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

የተዘረጋው የዲጂታል ሥርዓት ሁሉንም አሳታፊ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ዳያስፖራው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ይበልጥ ተሳታፊ እንዲሆን ያስችለዋል ብለዋል።

ችግኞች መትከል የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥን ለማቋቋም ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም በመርሃ ግብሩ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

ሌሎችም የዳያስፖራ አባላቶች ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሰል ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በእንግሊዝ፤ ለንደን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበር አስተባባሪ አቶ እንድሪስ መሐመድ በበኩላቸው በዲጂታል ሥርዓት ችግኞችን ባሉበት ሆነው በመከታተልና በአካባቢው ሰዎችን አሰማርቶ የእንክብካቤ ሥራ እንዲሰራ መደረጉ ተሳትፎው ቀጣይነት እንዲኖረው ይረዳል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ ዛሬ ዳያስፖራዎቹ የተንከባከቧቸው ችግኞች አምና በታላቁ የአገርቤት ጥሪና ከኢድ እስከ ኢድ መርሃ ግብሮች ዳያስፖራው የተከላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

መርሃ ግብሩ የተዘጋጀው የተተከሉ ችግኞችን ያሉበትን ሁኔታ እንዲያዩና የመንከባከብ ሥራ እንዲያደርጉ መሆኑን ገልጸው የዳያስፖራ አባላቱ ችግኞችን ለመንከባከብ አዲስ በተዘረጋው የዲጂታል ሥርዓት በመጠቀም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

ከ52 የዲያስፖራ አደረጃጀቶች የተወጣጡ ከ40 በላይ የሚሆኑ ዲያስፖራዎች በዛሬው ዕለት ችግኖችን የመንከባከብ ሥራ ማከናወናቸውን ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም