የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የአካባቢ ምህዳርን ከመቀየር አልፎ ገቢ ማመንጨት መጀመሩ ተጠቆመ

343

ወልዲያ፣ ጥር 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የአካባቢያቸውን ስነ ምህዳር ከመቀየር አልፎ ገቢ ማመንጨት መጀመሩን የሰሜን ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ።

አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራው ውሎ አድሮ እየሰጠ ባለው ጥቅም በኑሯቸው ለውጥ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

 

የላስታ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አበበ ወዳጅ ''የተፈጥሮ ሃብት ስራ ውጤታማ በመሆኑ ከእርሻ ስራ በተጨማሪ ገቢዬ እንዲሻሻል መሰረት ሆኖኛል'' ብለዋል። 

በዚህም በአካባቢው በለማ ተፋሰስ ውስጥ 150 የንብ ቀፎ በማበጀት በዓመት ከ4 እስከ 5 ኩንታል ማር በማምረት ከእርሻ ስራ ጎን ለጎን በሚያገኙት ገቢ በኢኮኖሚ የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል። 

ስለሆነም የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ከመቀየር ባለፈ የገቢ ምንጭ በመሆኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት አስታውቀዋል። 

የመቄት ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር በለጠ ፀጋው በበኩላቸው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው መገንዘባቸውን ጠቅሰው፤ የተፋሰስ ልማት የተከናወነባቸውን ቦታዎች ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በማድረግ የደረቁ ምንጮች ውሃ ማመንጨት መጀመራቸውን ገልጸዋል። 

እጽዋቶችም በመልማታቸው በለሙ ተፋሰሶች ውስጥ የእንስሳት መኖ በማጨድ ዓመቱን ሙሉ ያለችግር ለእንስሳት ቀለብ እያገኙ እንደሆነ ተናግረዋል። 

መልሰው የፈለቁ ምንጮችም ለሰውና ለእንሳት መጠጥነት ከማገልገላቸውም በላይ ለመስኖ ለሚያለግሉ ወንዞች ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የተፈጥሮ ሃብት ስራ የአካባቢያችንን ስነ ምህዳር ከማስጠበቅ ባለፈ የህዳሴ ግድባችን በደለል እንዳይሞላ በማሰብ ጭምር ነው ያሉት የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ዳሳሽ በቀለ፤ አርሶ አደሩ የተፋሰስ ልማት ላይ ግንዛቤው ማደጉን ጠቁመዋል። 

የተፋሰስ ልማት ባመጣው ውጤት የእንስሳት መኖ ፍላጎት እየተሟላ ከመሆኑም በላይ ደኖች እየለሙ በመምጣታቸው የአየር ሁኔታው መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።

This image has an empty alt attribute; its file name is %E1%89%B0%E1%8D%8B%E1%88%B0%E1%88%B54.jpg

 ከዚህም ሌላ አካባቢያችን የአባይ ተፋሰስ አካል በመሆኑ የምንሰራው የተፈጥሮ ሃብት ስራ ግድባችን በደለል እንዳይሞላ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል። 

በሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያ አቶ አያሌው ከበደ በበኩላቸው ቀደም ባሉት ዓመታት በለሙ ተፋሰሶች ውስጥ ለ8 ሺህ 790 ወገኖች የገቢ ምንጭ መፍጠሩን ገልፀዋል።

 በለሙ ተፋሰሶች የገቢ ምንጭ የተፈጠረውም በችግኝ ማፍላት፤ በመኖ ዘር ማሰባሰብ፣ በደን ልማትና በንብ ማነብ ሥራ የተሰማሩ ወገኖች ናቸው ብለዋል።

 የእነዚህ ተጠቃሚዎች ከምርት ሽያጭ ዓመታዊ ገቢያቸውም እስከ 70 ሚሊዮን ብር ይደርሳል ሲሉ ገልፀዋል። 

ይህን ስራ ለማስፋትና ህብረተሰቡ የባለቤት ስሜት ኖሮት ስራውን ባህሉ እንዲያደርግም 6 ሺህ የሚደርሱ አርሶ አደሮችን በ690 በተፋሰስ ተጠቃሚዎች ህብረት ሥራ ማህበር እየተደራጁ መሆኑን አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም