ሙስናና ብልሹ አሰራሮች የወለዷቸው የመልካም አስተዳደርና የኑሮ ውድነት ችግሮች መፈታት አለባቸው--የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች

203

ጋምቤላ ጥር 20 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- ሙስናና ብልሹ አሰራሮች የወለዷቸው የመልካም አስተዳደርና የኑሮ ውድነት ችግሮችን እንዲፈቱላቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

“ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለብልፅግና ጉዟችን ስኬት’’ በሚል መሪ ሃሳብ  የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎቹ፤ በተለይም ህዝቡን እየፈተኑ ያሉትን የኑሮ ውድነት፣ ሌብነት የሙስናና ብልሹ አሰራር ችግሮችን እንዲፈቱ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

አቶ ማቲዎስ መሰኒ በሰጡት አስተያየት፤ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ አካባቢ የነበረውን ችግር በሽምግልና በመፍታት የሀገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ ያደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም ህዝቡን በከፍተኛ ደረጃ እያማረረ ያለውን የኑሮ ውድነት ችግር በመፍታት ረገድ ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ያለውን የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ደረጃ እያባባሰ ያለው ከነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ጋር የተያያዘ የብልሹ አሰራር ችግሮች መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ  አቶ ኳት ቲያንግ ናቸው።

መንግስት በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት፣ በመልካም  አስተዳደርና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሌላው ተሳታፊ ፓስተር ኡቦንግ ኡሎም በበኩላቸው፤ መንግስት ዘላቂ ሰላምንና ልማትን ለማረጋጥ ለጀመራቸው ስራዎች መቃናት የኃይማኖት ተቋማት ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግስት አሁንም በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሃይማኖትና ከብሄርተኝነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኩዌይ ጆክ ከተሳታፊዎች የተነሱትን ጥያቄዎች አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ከነዳጅ ጋር ተያይዞ የተነሳው ጉዳይ አግባብነት ያለውና በቀጣይ በትኩረት የሚሰራበት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከል የጥናትና ምርምር ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል፤ በህዝቡ የተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳድር ጥያቄዎች በታቀደ መልኩ ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በድል በመሻገር የተጀመረውን የለውጥና የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ያሉት ደግሞ የትራንስፓርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ በሩ ናቸው።

በተለይም በአመራሩ ዘንድ የሚታዩ የብልሹና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ናቸው

በአሁኑ ወቅትም የአመራሩ የስድስት ወር የእቅድ አፈፃፀምን በግምገማ ችግሮችን የማጥራት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮችን በመታገል ረገድ የህዝቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ወጣቶች ፣ ሴቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ከስፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም