በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች በጥሩ የቡድን መንፈስ ዝግጅት እያደረግን ነው - አትሌቶች

178

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 20/2015 "በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች በጥሩ የቡድን መንፈስ ዝግጅታችንን እያደረግን እንገኛለን" ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሳታፊ አትሌቶች ገለጹ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ለሻምፒዮናው ዝግጅት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።

44ኛው የዓለም የአገር አቋራጭ ሻምፒዮና የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም በአውስትራሊያ ባትረስት ከተማ ይካሄዳል።

በሻምፒዮናው ከ60 አገራት የተውጣጡ ከ550 በላይ የዓለማችን እውቅ ስፖርተኞች በተለያዩ የውድድር ዓይነቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

በዚህ የውድድር መድረክ ላይ ለአሸናፊነት ከሚጠበቁ ስፖርተኞች መካከል የኢትዮጵያ አትሌቶች ይገኙበታል።

ከውድድሩ ተሳታፊ አትሌቶች መካከል አትሌት ጌትነት ዋለ እና አትሌት ብርቄ ሐይሎም በሻምፒዮናው ጥሩ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በአትሌቲክስ ቡድኑ ጥሩ የሚባል የቡድን መንፈስ እንዳለ እና በሻምፒዮናው የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚሮጡ ተናግረዋል።

ከቡድኑ አሰልጣኞች መካከል ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ፤ በውድድሩ የሚሳተፉት ልምድ ያላቸውና ወጣት አትሌቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለውድድሩ በቂ ዝግጅት እያደረጉ ነው ብለዋል።

በዚህ ውድድር የሚካፈሉ የተለያዩ ሀገራት አትሌቶች ለአሸናፊነት የሚመጡ ቢሆንም ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች የበላይ ሆኖ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአትሌቶቹ ዝግጅት ውድድሩ የሚካሄድበትን ሀገር አየር ንብረት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አሰልጣኝ ኢንስፔክተር ደሳለኝ ፀጋ ናቸው።

የቡድኑ የአንድነትና የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲሁም የአሸናፊነት መንፈስ ጠንካራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ዮሐንስ እንግዳ እንደገለጹት፤ በሻምፒዮናው የሚካፈሉ አትሌቶች ከጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሆቴል ተሰባስበው በጋራ ልምምድ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በአትሌቲክሱ ዘርፍ እየተመዘገበ የሚገኘውን መልካም ውጤት ለማስቀጠል በማሰብ ፌዴሬሽኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

ፌዴሬሽኑ ለሻምፒዮናው በሚገባ ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊውን ግብዓት እያሟላ እና የቅርብ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

አትሌቶቹ በመልካም የጤንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ነው አቶ ዮሐንስ የገለጹት።

በዚህ ውድድር የሚሳተፉ አትሌቶች ታኅሳስ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በሱሉልታ በተካሄደው 40ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በቀጣዩ ወር የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም በሚካሄደው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በአዋቂ ወንዶችና ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ውድድር፣ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ሴቶች 6 ኪሎ ሜትር እና በ8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ዱላ ቅብብል(ሪሌ) የምትካፈል ይሆናል።

በሻምፒዮናው ላይ ተጠባባቂዎችን ጨምሮ 28 አትሌቶች በሆቴል ከትመው ልምምድ እያደረጉ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም