በኢትዮጵያ የተከፈተውን የሰላም ምዕራፍ ለማጽናትና ለመልሶ ማቋቋም ሥራ ድጋፍ እናደርጋለን- ዳያስፖራዎች

182

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 20 ቀን 2015 በኢትዮጵያ የተከፈተውን አዲስ የሰላም ምዕራፍ ለማጽናትና ለመልሶ ማቋቋም ሥራ ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ በእንግሊዝና ካናዳ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ገለጹ።

ዳያስፖራዎቹ አገር በፈተና በወደቀችበት ወቅት ከጎን በመሆን ሲያከናውኑት የቆዩትን ሥራ አሁን ደግሞ በሰላም ግንባታና በልማት ሥራዎችም ለመደገፍ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ከእንግሊዝ አገር የመጡት አቶ ዘላለም ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች በእንግሊዝ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገር በተፈተነችበት ወቅት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ አዲስ የሰላም ምዕራፍ መምጣቱን ገልጸው፤ ይህ የተጀመረውን ሰላም ማጽናት እና መደገፍ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድርሻ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የሰላም አውዱን ዘላቂ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረው፤ በመልሶ ማቋቋምና መልሶ ግንባታ የተጀመሩ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት።

ሌላኛው ከካናዳ ኦታዋ የመጡት አቶ አሌክሳንደር ስሞኦን በበኩላቸው፤ በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ሁለንተናዊ ልማት ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ይህ ድጋፍ በሰላም ማጽናትና መልሶ ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ በተለይ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ዓርማ ለሆነው ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

በተመሳሳይ ከካናዳ ኦታዋ የመጡት ሌላኛው ዳያስፖራ አቶ ሰማነህ ታምራት፤ ዳያስፖራው ባለው አቅም ሁሉ ለአገሩ ሁለንተናዊ ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

በተለይ በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው በኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራት የሚሹ እንዳሉ ገልጸው፤ አሁን የመጣው የሰላም አየር ለዚህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በመሆኑም እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መጥተው መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ መንግሥት ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም