በኮንስትራክሽን ግብዓቶችና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ያተኮር ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ሊካሄድ ነው

70
አዲስ አበባ መስከረም 24/2011 በኮንስትራክሽን ግብዓቶችና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረቱን ያደረገው '9ኛው አዲስ ቢውልድ' ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3 ቀን 2011 በአዲስ አበባ ሚሊኒዬም አዳራሽ ሊካሄድ ነው። ኤግዚቢሽኑን የሚያዘጋጁት ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና ከኤቴል ማስታወቂያና ኮሙኒኬሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ኤግዚቢሽኑን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል። በሚኒስቴሩ የኮንስትራክሽን ምክር ቤትና ባለድርሻ አካላት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ንጉሴ እንደተናገሩት፤ ኤግዚቢሽኑ የቴክኖሎጂ የልምድ ልውውጥና የእውቀት ሽግግር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል። የገበያ ትስስርና የስራ ግንኙነት ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከመፍጠር ባለፈ የግንባታ ዘርፉን የሚያነቃቃና ለአምራቾች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ይጠበቃል። የኮንስትራክሽን ግብዓትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለአገር ውስጥ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች፣ ለዘርፉ መንግስታዊ ተቋማትና ለኢንዱስትሪ ባለሙያዎች የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል። በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ረገድ ለኢንቨስትመንት ያሉትን ምቹ ሁኔታዎችና በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ጉዞ ላይ ከግብዓት አቅርቦት አንጻር የገጠሙ ፈተናዎችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚያተኩር የፓናል ውይይት መድረክ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። በአገሪቱ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን ለማስተዋወቅና ኢንቨስተሮችን በስፋት ተሳታፊ ለማድረግ ኤግዚቢሽኑ ጥሩ ሁኔታ እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መኮንን ኃይሉ ተናግረዋል። ''ኢንቨስተሮች በአገሪቱ ባለው የተፈጥሮ ኃብት በመጠቀም ለአገሪቱ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ኤግዚቢሽኑ ሊያግዝ ይችላል'' ብለዋል። ''ባለፉት ከተካሄዱት ኤግዚቢሽኖች ልምድ ተገኝቶበታል፣ በዚህ ዓመትም የተሻለ ይሆናል'' ያሉት ደግሞ የኤግዚቢሽኑ አዘጋጅ የኢቴል ማስታወቂያና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ወይዘሮ ሀይማኖት ተስፋዬ ናቸው። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ በስፋት በመምጣት ላይ ናቸው፣ ይህም ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ መሆኑን ገልጸዋል። በኤግዚቢሽኑ ላይ ከኢትዮጵያ፣ ግሪክ፣ ጣሊያን፣ ቱርክ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አገሮች በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያሳዩ ከ80 በላይ ኩባንያዎች ይሳታፋሉ። በኤግዚቢሽኑ ላይ ከ5 ሺህ በላይ ጎብኝዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም