ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር በመተባበር ወደ ውጭ አገራት ለስራ የሚሰማሩ ሙያተኞች የተሻለ ክህሎት እንዲኖራቸው እየተሰራ ነው

155

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 20/2015 ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር በመተባበር ወደ ውጭ አገራት ለስራ የሚሰማሩ ሙያተኞች የተሻለ ክህሎት እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ከክልልና ከተጠሪ ተቋማት ጋር የ2015 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ውይይት አካሂዷል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ የሚሰማሩ ዜጎች በቂ የክህሎት ስልጠና እንደማይሰጣቸው አስታውሰዋል፡፡

ይህም ዜጎች ልፋታቸውን የሚመጠን ጥቅም ካለማግኘታቸውም በላይ ለአስከፊ የመብት ጥሰት እንዲጋለጡ እድል ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚገኙ 77 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የክህሎት ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ለዚህም የስርዓተ ስልጠና ክለሳ እና የማሰልጠኛ መሳሪያ ዝግጅት እንደተከናወነ ነው የገለጹት።

የአረብኛና እንግሊዘኛ ቋንቋ ስርአተ ስልጠና ተዘጋጅቶ በውጭ አገር ለሚሰማሩ ዜጎች እንደሚሰጥም አብራርተዋል፡፡

ከዚህም ቀደም በሙከራ ደረጃ በነርስና ግብርና ዘርፍ ላይ የውጭ አገር የስራ ስምሪት መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በዚህም ጥሩ ልምድ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

በተለያዩ አገራት ያለውን የስራ ገበያ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ከባህሬን፣ ኦማን፣ ጣሊያን፣ ዮርዳኖስ፣ ጀርመን፣ ኩዌት፣ ባህሬንና ሊባኖስ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ሰነድ ለመፈራረም ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ ከጃፓን፣ እስራኤልና ሳውዲ አረቢያ አገራት ጋር የድርድር ሰነድ የማዘጋጀት ሂደት መጀመሩ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም