በላሊበላና ቆቦ ከተሞች በፀሐይ ሃይል ቴክኖሎጂ ህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተቻለ

222

ባህር ዳር ፤ ጥር 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) ፡- በላሊበላና ቆቦ ከተሞች 38 ሚሊየን ብር በሆነ ወጪ በፀሐይ ሃይል ቴክኖሎጂ ህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጅ ቢሮ አስታወቀ።

በነበረው ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች በላቀ ቴክኖሎጂ ዘላቂነት ያለው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወንድአጥር መኮንን ለኢዜአ ተናግረዋል። 

እየተሰራ ካለው ውስጥም በቆቦ ከተማ በ22 ሚሊየን ብር በጀት በፀሐይ ሃይል ቴክኖሎጂ ከጉድጓድ 60 ሊትር ውሃ በሰኮንድ የመግፋት አቅም ያለው መሰረተ ልማት ግንባታው በማጠናቀቅ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል። 

በላሊበላ ከተማም 16 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው ደግሞ 25 ሊትር በሰኮንድ ውሃ የመግፋት አቅም ያለው መሆኑን አስረድተዋል።  

ከጉድጓድ በመሳብ በቧንቧ መስመር አማካኝነት ለማሰራጨት በሁለቱ ከተሞች የተገነቡት የውሃ መሰረተ ልማቶች ከ140 ሺህ በላይ ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። 

የፀሐይ ሃይል ቴክኖሎጂ ግንባታው ጥቅም ላይ መዋሉም ቀደም ሲል በኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ምክንያት የሚፈጠረውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በማስቀረት የከተሞቹን ነዋሪዎች በዘላቂነት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። 

በከተሞቹ የነበረው የፀጥታ ችግር ከተፈታ ጊዜ ጀምሮ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦቱን በጀነሬተር በመግፋትና በቦቲ ውሃ ይቀርብ እንደነበር አውስተዋል። 

ከተሞቹን በፀሐይ ሃይል ለሚሰራው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግም ዩኒሴፍና የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይም ቴክኖሎጂውን ወደ 20 ከተሞች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ሃላፊው አስረድተዋል። 

በሰሜን ወሎ ዞን የቆቦ ከተማ አስተዳደር የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገበያው አማረ በበኩላቸው፤ በነበረው ችግር የከተማዋ የውሃ መሰረተ ልማት ጉዳት ደርሶበት መቆየቱን አስታውሰዋል።

ጉዳት የደረሰባቸውን የውሃ ተቋማት በመጠገን በሁለት ቀናት ፈረቃ ውሃ ሲቀርብ የነበረው አሁን ላይ የፀሐይ ሃይልን በመጠቀም ስርጭቱን ማሻሻል መቻሉን ተናግረዋል። 

ከላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አበባው አመሬ በሰጡት አስተያየት፤ በከተማው ባለፉት ጊዜያት በነበረው ችግር የውሃ አቅርቦት ተቋርጦባቸው መቆየቱን አውስተዋል። 

በዚህም ምክንያት ረጅም ርቀት በመሄድ ንፅህናውን ያልጠበቀ የወንዝ ውሃ ለመጠቀም ተገደው እንደነበርና ችግሩን ለመፍታት መንግስት በጀነሬተርና በቦቴ ለማቅረብ ጥረት ማድረጉን ጠቁመዋል። 

ከሰሞኑ የተሟላ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር የፀሐይ ሃይል ቴክኖሎጂን መጠቀም በመቻሉ ችግሩ መቃለሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም