በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ8 ሺህ 800 በላይ ለሚሆኑ ምርትና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ ተሰጥቷል - የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት

305

አዲስ አበባ ጥር 19/2015(ኢዜአ) በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከ8 ሺህ 800 በላይ ለሚሆኑ ምርትና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ መስጠቱን የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ አገራዊና ሌሎች ደረጃዎች ላይ የተቀመጡ የጥራት መስፈርቶችን ማሟላታቸውንና አለማሟላታቸውን የማረጋገጥ ስራ ማከናወን ዋንኛ ተግባሩ ነው። 

በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃዎች መሰረት ለምርትና አገልግሎቶች በአስገዳጅና በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የላቦራቶሪ ፍተሻ፣ የኢንስፔክሽንና የሰርቲፊኬሽን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። 

የድርጅቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ተክኤ ብርሃነ ከ8 ሺህ 800 በላይ ምርትና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት መሰጠቱን ለኢዜአ ገልጸዋል። 

ይህም ተቋሙ በዕቅድ ከያዘው 9 ሺህ 935 ጋር ሲነጻጸር ከ88 በመቶ በላይ አፈጻጸም ያለው ነው ተብሏል።

በጥራት ፍተሻ ላቦራቶሪ፣በቁጥጥርና የጥራት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት(ሰርተፊኬሽን) ለ766 የገቢ፣ ለ717 የወጪ ምርት ናሙናዎች እና ለሌሎች ዘርፎች የጥራት ማረጋገጫ መሰጠቱን ነው አቶ ተክዬ የተናገሩት።  

የአፈር ማዳበሪያ፣ስንዴ እና የምግብ ዘይት የጥራት ማረጋገጫ ከተሰጠባቸው ምርቶች መካከል ይገኙበታል።

 እንደ አቶ ተክኤ ገለጻ፤ ድርጅቱ ለላኪዎች፣ አስመጪዎችና አምራቾች ምርቶችን ከማምረት ጀምሮ እስከ ማጓጓዝ የሶስተኛ ወገን የኤንስፔክሽን አገልግሎት እየሰጠ ነው።

 የሰርቲፊኬሽን አገልግሎት ያገኙ ተጠቃሚ አምራች፣ አስመጪዎችና ላኪዎች የገበያ ድርሻቸውን ማስፋት መቻላቸውን ገልጸዋል። 

ይህ መሆኑ የኢትዮጵያ ምርቶች በውጭ ገበያ ላይ ተመራጭና ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋቸውና የውጭ ምንዛሬም ለአገሪቱ እንደሚያስገኝም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት። 

ድርጅቱ እየሰጠ ያለው የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገትን ከማፋጠን ባሻገር ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።  

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በአዲስ አበባና በክልል በሚገኙ ስምንት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና በጂቡቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም