በሐዋሳ ሐይቅ የሕገወጥ አስጋሪዎች መበራከት የፈጠረውን የዓሳ ሀብት መመናመን አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ተገለጸ

274

ሀዋሳ ጥር 19/2015 (ኢዜአ) በሐዋሳ ሐይቅ የሕገወጥ አስጋሪዎች መበራከት የፈጠረውን የዓሳ ሀብት መመናመን አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያሻው በሐይቁ በዓሳ ማስገር የተሰማራ ማህበር አመለከተ።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የግብርና መምሪያ በበኩሉ "ሕገወጥ ማስገር ለመከላከል የሚያስችል ስራ እያከናወንኩኝ ነው" ሲል ገልጿል።

የሐዋሳ ሐይቅ የዓሳ አስጋሪዎች መሰረታዊ ሁለገብ የሕብረት ስራ ማህበር በሐይቁ ላይ አሳ ማስገር የጀመረው በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1960ዎቹ አካባቢ ነበር።

በወቅቱ የተጠቃሚ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ያሰገረውን ዓሳ በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች በማዞር ይሸጥ እንደነበር የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ዳዊት አብርሀም ይገልጻሉ።

በጊዜ ሂደት የአሳ ፍላጎት መጨመርን ተከትሎ የአስጋሪዎች ቁጥርም እያደገ መጥቶ በ1989 ዓ.ም ማህበሩ 105 አባላትን በመያዝ እንደገና በአዲስ መልክ መደራጀቱን ተናግረዋል።

በከተማዋ መስፋትና የነዋሪው ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የዓሳ ፍላጎት በማደጉና ማህበሩ ባሉት አባላት ብቻ አሳ ማቅረብ ባለመቻሉ በአሁኑ ወቅት የአባላቱ ቁጥር ከ495 በላይ ደርሷል።

ማህበሩ ከ70 በላይ ጀልባዎችን በመጠቀም ዓሳ የማስገር ስራውን በማከናወን ላይ ይገኛል ነው ያሉት አቶ ዳዊት።

በአሁኑ ወቅት የሕገወጥ ዓሳ አስጋሪዎች መበራከትና የማይፈቀድ መረብን በመጠቀም ጫጩት አሳዎችን ጭምር በማስገራቸው ምክንያት በሐይቁ የዓሳ ሀብት መጠን እንዲመናመን ማድረጉን አመልክተዋል።

በሐይቁ ላይ እየተፈጸመ ያለው ሕገወጥ አሳ የማስገር ተግባር ሀብቱ እንዲመናመን ከማድረጉ ጋር ተዳምሮ በማህበሩ ስራ ላይ ጫና መፍጠሩንም እንዲሁ።

የሚመለከተው አካል በሐይቁ ላይ የሚፈጸም ሕገወጥ ዓሳ የማስገር ተግባርን በማስቆም ሀብቱን ከጥፋት ሊታደግ እንደሚገባ አቶ ዳዊት ጠይቀዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ የእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ብርሀኑ ቢንቤ የሕገወጥ አስጋሪዎች መበራከት እና የጫጩት አሳ ማስገር ለአሳ ሀብት መመናመን ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ዋንኞቹ ናቸው ይላሉ።

በሐይቁ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመከላከል እየተከናወነ ካለው ሕገወጦችን የመቆጣጠር ስራ በተጨማሪ የሕጋዊ ማህበሩ አባላትን በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ በማድረግ የአስጋሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አባላቱ ዓሳ በኩሬ ውስጥ እንዲያረቡ ለማድረግ መታሰቡን ተናግረዋል።

ሕገወጥ ዓሳ የማስገር ተግባርን ከመከላከል አንጻር ጉድለቶች አሉ ያሉት ዳይሬክተሩ ችግሩን በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዓሳ ምርምርና ትምህርት ማዕከል ኃላፊ ዶክተር ካሳዬ ባልከው በበኩላቸው በተለያዩ ጊዜያት በተከናወኑ ጥናቶች በሐይቁ የዓሳ ሀብት መመናመን ችግር እያጋጠመ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል።

የዓሳ ሀብት መመናመንን ለመታደግ ሕገወጦችን የመከላከል ስራ በተቀናጀ መንገድ ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።

ከሐዋሳ ሀይቅ ቀደም ሲል በዓመት ይመረት የነበረው ከ1 ሺህ ቶን በላይ ዓሳ በአሁኑ ሰዓት ወደ 400 ቶን ዝቅ ማለቱን ከከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም