መንግስት በሰውሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ የሚመጣን መፈናቀል ለማስቀረት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው

110

አዲስ አበባ ( ኢዜአ) ጥር 19 /2015 መንግስት በሰውሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ የሚመጣን መፈናቀል ለማስቀረት ብሎም አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ጉዳቱን ለመቀነስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ አማካሪ ሮበርት ፓይፐርን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ውይይቱ የሀገር ውስጥ መፈናቀልን በዘላቂነት ለማስቀረት እየተሰሩ ባሉ ስራዎችና አደጋው ሲከሰት ለመከላከል እየተገበሩ ባሉ ስትራቴጂዎች ላይ ያተኮረ ነው።

መንግስት በሰውሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ የሚመጣን መፈናቀል ለማስቀረት ብሎም አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ጉዳቱን ለመቀነስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ችግሩ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሄን ለማምጣት የሚረዱ የልማት ስራዎች ላይ በማተኮር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ተደጋጋሚ ድርቅ በሚከሰትባቸው የአርብቶ አደር አካባቢዎች የውሃ ፣ የመስኖ ፣ የጤና እና የትምህርት ልማት ስራዎች በስፋት እየተተገበሩ እንደሚገኝም ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ለሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ እና ሁሉንም ባለድርሻ ተቋማት የያዘ ምክር ቤት ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የመንግስትን ጥረት አለም አቀፍ አጋር አካላት እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ የሃገር ውስጥ ተፈናቃይ ልዩ አማካሪ ሮበርት ፓይፐር በበኩላቸው ተቋማቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።

ለሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄን በመስጠት ረገድ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው ተግባር ለሌሎች ሃገራትም በመልካም ተሞክሮነት ሊወሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የመንግስትን ሁሉን አቀፍ ጥረቶች በፋይናንስ እና አቅም ግንባታ መስክ ለመደገፍም ቃል ገብተዋል።

በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከመንግስት የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች በሶማሌ ክልል ጉብኝት በማድረግ ለሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚደረጉ ድጋፎችን የተመለከቱ ሲሆን በአዲስ አበባም ተቀማጭ ከሆኑ የአህጉራዊና አለምአቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች ጋርም ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም