የ12ተኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 29 ሺህ 909 ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ ውጤት አምጥተዋል

312

አዲስ አበባ ጥር 19/2015 (ኢዜአ) የ2014 የ12ተኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ ተፈታኞች ውስጥ 29 ሺህ 909 ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

ትምህርት ሚንስቴር በ2014 ዓ.ም የ12ተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት፣ የውጤት ትንታኔ የዩንቨርስቲ ቅበላ ምደባና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የዚህ አመት የፈተና ውጤት በተአማኒነቱ ለወደፊቱ መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።

የ 2014 የ 12 ተኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ ተፈታኞች ውስጥ 29 ሺህ 909 ተማሪዎች ከ 50 በመቶ በላይ አስመዝግበዋል ብለዋል።

ይህም በመቶኛ 3.3 መሆኑን ገልጸዋል።

የተገኘው ውጤት ለአመታት ሲንከባለሉ የቆዩ የበርካታ ችግሮች መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ተሸፍኖ የቆየውን የትምህርት ስርአት ያለበትን ደረጃ የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ከ 50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ወደ ዩንቨርሲቲ የሚገቡ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ለዚህ አመት ብቻ በቀጣይ በሚደረግ አዲስ የልየታ ስራና የዩንቨርሲቲዎች የመቀበል አቅማቸውን ከግምት በማስገባት ደካማ ውጤት ያስመዘገቡበት የትምህርት አይነቶችን መልሶ ፈተና እንዲወስዱ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

በሀገር ደረጃ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት በተፈጥሮ ሳይንስ 666 እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 524 ሆኖ መመዝገቡን ተናግረዋል።

በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ፈተናውን አስመልክቶ የሚሰራጩ መረጃዎች ከእውነት የራቁ መሆኑን ገልጸዋል።

ለ 2014 የ 12ተ ኛ ክፍል ፈተና ከ ከ 985 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና መቅረባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም