ለዳያስፖራ አደረጃጀቶች የተሰጠው እውቅና ለአገራቸው በጎ ስራ እየሰሩ ለሚገኙ ሁሉ ነው-ፕሬዚደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ

155

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 18/2015 ለዳያስፖራ አደረጃጀቶች የተሰጠው እውቅና ለአገራቸው በጎ ስራ እየሰሩ ለሚገኙና በመላው ዓለም ላሉ የዳያስፖራ አባላት ሁሉ ነው ሲሉ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

የመጀመርያው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አደረጃጀቶች የእውቅና መርሃግብር ፕሬዚደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ዛሬ ተከናውኗል ።

May be an image of 1 person and standing

በዚህም ወቅት በሁለንተናዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጎ ተሳትፎ ያደረጉ እና ከ25 አገራት የተውጣጡ 52 የዳያስፖራ አደረጃጀቶች እና አባላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እውቅናው ለአገራቸው በጎ ስራ እየሰሩ ለሚገኙና በመላው ዓለም ላሉ የዳያስፖራ አባላት ሁሉ ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቷ አክለውም ኢትዮጵያ ለአገራቸው መልካም ነገር የሚያከናውኑ አካላትን ሁሌም እንደምታስታውስ ገልጸው መንግስትም ዳያስፖራው ከአገሩና ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ነው ያሉት።

አገሪቱ ያለፉትን ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማለፏን ያስታወሱት ፕሬዚደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በሰላም ግንባታና በመልሶ ማቋቋም ስራ ላይ አገሩን እና ህዝቡን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው በመላ አለም የሚገኙ የዳያስፖራ አባላቶች ኢትዮጵያ ችግርና ፈተና በገጠማት ጊዜ ለአገራቸው ያሰሩት ስራ በወርቃማ ብዕር የሚፃፍና ሁሌም በታሪክ የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ ከዚህ ቀደም በአገር ሁለንተናዊ ተግባራት ላይ የነበረውን ተሳትፎ ይበልጥ በማሳደግ በአገሪቱ እየተከናወነ ባለው የሰላም ግንባታ ላይም በጎ ሚናውን በመወጣት የአገር አለኝታነቱን ዳግም እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ በበኩላቸው ዳያስፖራው ማህበረሰብ ለአገሩ በተለያዩ መልክ እያሳየ ላለው ተሳትፎ መንግስት ሁሌም እውቅና እንደሚሰጥና ተመሳሳይ መድረኮች ከዚህ በኋላም ተጠናክሮ እንደሚካሄድ አረጋግጠዋል።

የመጀመርያው የዳያስፖራ አደረጃጀቶች የእውቅና መርሃግብር በተካሄደበት መድረክ የሁሉንም ዳያስፖራ ማህበራት ማህደር የያዘ መፅሀፍ በይፋ መመረቁን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም