ሚኒስቴሩ የዲፕሎማሲ ስራውን የሚያቀላጥፍ የመዋቅር ማሻሻያና የሰው ኃይል ድልድል ጀምሯል

131
አዲስ አበባ መስከረም 24/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፕሎማሲ ስራውን ለማቀላጠፍ የመዋቅር ማሻሻያና የሰው ኃይል ድልድል መጀመሩን አስታወቀ። እርምጃው መስሪያ ቤቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ የሚያስችለው ነው ተብሏል። መስሪያ ቤቱ በአሁኑ ወቅት ስራውን የሚከውነው ከስምንት ዓመታት በፊት በተዘረጋ መዋቅር አማካኝነት ነው። ይህ ደግሞ አሁን ያለው የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት አሰራር ከደረሰበት እድገትና ከሚጠይቀው አሰራር ጋር የተጣጣመ አይደለም። በመሆኑም የመስሪያ ቤቱ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚሻውን መዋቅር፣ የአሰራር ሰርዓትና የሰው ኃይል መሰረት ያደረገ የመዋቅር ማሻሻያ ማድረግ ይቻል ዘንድ ላለፉት ስምንት ወራት ጥናት ሲደረግ መቆየቱ ተገልጿል። የሚኒስቴሩ ቃል-አቀባይ አቶ መለስ አለም ጉዳዩን አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የአዲሱ መዋቅር ጥናት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጽደቁ ኮሚቴ ተቋቋሞ የሰው ኃይል ድልደላ እየተካሄደ ነው። ዋና ዓላማው 'ስራና ሰራተኛን ማገናኘት ነው' የተባለለት የመዋቅር ማሻሻያው የሚመለከተው በውጭ አገራት የተሰማሩ የሚሲዮን እና  የዋናው መስሪያ ቤት ሰራተኞችን መሆኑን ገልጸዋል። በዚሁ መሰረት በተለያዩ የውጭ አገራት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ተመድበው የሚሰሩ 90 የአገልግሎት ሰራተኞች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ጥሪ ተደርጎላቸዋል ብለዋል። በአዲሱ ስምሪትም ''ሙያዊ ብቃታቸው ከፍ ያለ፣ ተናግረው የሚያሳምኑና ተከራክረው በመርታት የአገራቸውን ጥቅም የሚያስከብሩ ሰራተኞች ተገቢው ቦታ ላይ ይመደባሉ'' ሲሉ አቶ መለስ አብራርተዋል። ምደባው ለምጣኔ ኃብታዊ ጉዳዮችና ለጎረቤት አገራት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም ነው ቃል-አቀባዩ የተናገሩት። በሚዘረጋው አዲስ መዋቅር ከወትሮ በተለየ መልኩ በሚኒስትር ዴኤታ ደረጃ አራት ሰዎች እንደሚመደቡና ከነሱም ቀጥሎ ቋሚ ተጠሪ ጽህፈት ቤት የሚባል የስልጣን እርከን እንደሚጨመር ገልጸዋል። ከሚኒስትር ዴኤታዎቹ አንዱ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና የዳያስፖራ ጉዳዮችን፣ ሁለቱ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ጉዳዮችን የሚመሩ ሲሆኑ አንዱ ደግሞ የሃብት አስተዳደር አገልግሎት ላይ በትኩረት የሚሰራ ይሆናል ነው ያሉት። ከእነሱ በመቀጠል የዕለት ስራዎችን የሚከታተሉና ውሳኔዎችን የማስተላለፍ ስልጣን ያላቸው ቋሚ ተጠሪ ጽህፈት ቤቶችን የሚመሩ አምስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንደሚኖሩም ጠቅሰዋል። አዲሱ መዋቅር በመስሪያ ቤቱ ባለሙያዎች የተሰራ ሲሆን ቱርክ፣ ጀርመንና ስዊዘርላንድን ጨምሮ የ20 ታላላቅ አገራትን ልምድ ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑም ተመልክቷል። የቃል አቀባዩ መግለጫ ኢትዮጵያ በ73ኛው የተመድ ጉባዔ ላይ የነበራት ተሳትፎና የተመዘገቡ ስኬቶች የተዳሰሱበትም ነበር። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የተመራው ልዑክ የተሳካ ተግባር ፈፅሞ መመለሱን አቶ መለስ ገልጸዋል። የምስራቅ አፍሪካ የሰላም ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ መደረጉን ከስኬቶቹ መካከል አንስተዋል። የተለያዩ አገራት መንግስታት በኢትዮጵያ ስላለው የለውጥ እንቅስቃሴ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉም ሌላው ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።       
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም