በርካታ ዕድሎችና ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ባሉት የጤናው ዘርፍ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

124

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 18/2015/ በኢትዮጵያ በርካታ ዕድሎችና ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ባሉት የጤናው ዘርፍ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ጥሪ አቀረቡ።

ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት "ኢንቨስት ኦሪጅን 2023 ፎረም" በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

መድረኩ በፌደራል መሬት ባንክ ልማት ኮርፖሬሽን የተዘጋጀ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2025 ኢትዮጵያን ከዓለም አምስት ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች አንዷ ለማድረግ የሚያስችሉ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያን አጓጊ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታዎች ለመቃኘት በዓለም አቀፍ መድረኮች የተመሰከረላቸው ባለሙያዎች ሀሳባቸውን እንዲለዋወጡ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና አለው ተብሏል።በተጨማሪም ኢንቨስተሮች እና የኢኮኖሚ ተዋናዮችን ለማግኘት የሚሰጠው ዕድል ከፍተኛ መሆኑ ነው የተገለጸው።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ኢንቨስት ማድረግ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ገልጸዋል።

በፋርማሲቲካል፣ በቴርሸሪና ሌሎችም ዘርፎች ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሃብቶች የፖሊሲ ማሻሻያ ከማድረግ በተጨማሪ ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች አሉት ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ በርካታ ዕድሎችና ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ባሉት የጤናው ዘርፍ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።

የመሬት ባንክ ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን በበኩላቸው፤ ፎረሙ በኢንቨስትመንት ረገድ የጋራ ጥቅም የሚገኝበት ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የፌር ፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀመንበር ዘመዴነህ ንጋቱ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት ለማድረግ በርካታ ባለሃብቶች ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የዕድገት አመላካቾች ሳቢ መሆናቸውን የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ ለዚህም አይ.ኤም.ኤፍ ያወጣው መረጃ ጥሩ አመላካች ስለመሆኑ አንስተዋል።

ለሁለት ቀን በሚካሄደው የኢንቨስት ኦሪጅን 2023 ፎረም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም