በግብርና ሥርዓተ ምህዳር ያሉ እምቅ ሃብቶች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ አላቸው- ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት

86

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 18/2015/በኢትዮጵያ የግብርና ሥርዓተ ምህዳር ያሉ እምቅ ሃብቶች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

"ዘርንና የምግብ ሥርዓት በዘላቂነት ለመጠበቅ የአነስተኛ ማሳ ባለቤት አርሶ አደሮች አስተዋጽኦና በብዝሃ ህይወት" ዙሪያ የሚመክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ ነባር የብዝሃ ህይወት ዝርያዎች መመናመንና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች በዓለም ላይ 1 ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የምግብ ዋስትና ችግር እንደገጠማቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማርዮ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብዝሃ ህይወት ጉልህ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በግብርና ሥርዓተ-ምህዳር ያሉ እምቅ ሃብቶችን በመጠበቅ የምግብ ዋስትናን ማረጋጋጥ ይገባል ብለዋል።

የተፈጥሮ እውቅት ለሳይንሳዊ እውቀት መሰረት መሆኑን ጠቅሰው ለምግብ ዋስትናም ድርሻው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

የተቀናጀ የምርምርና የማህበረሰብ ባዮካልቸራል ዳይቨርሲቲ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና መረጃዎችን በማውጣት ለአካባቢ ባህላዊ ዕውቀትና ለብዝሃ ህይወት ጥቅም መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በከፍተኛ የግብርና ስርዓተ ምህዳር ስር የሚገኙ በርካታ የብዝሀ ሕይወት ሃብቶች ያሏት ሀገር በመሆኗ ይህንኑ በሳይንስ በተደገፈ ምርምር በማጠናከር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የኑሮን ውድነት ለመቀነስ ከተለመደው አመጋገብ በመውጣት ሌሎች አማራጮችን መከተል ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም