የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የእምቦጭ አረምን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሄራዊ ስትራቴጂክ እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ገለጸ

295

ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 የእምቦጭ አረምን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ብሄራዊ ስትራቴጂክ እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የ2015 ዓ.ም ከደምበል/ዝዋይ ሓይቅ ላይ እምቦጭ አረምን ለማስወገድ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር የተመለከተ ውይይት በሻሸመኔ ከተማ ተካሂዷል። 

በዚህ ወቅት በሚኒስቴሩ የኢኮ ሀይድሮሎጂና የውሃ ጥራት ዴስክ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ዘሪሁን በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ከጣና ጀምሮ በስምጥ ሸለቆ በሚገኙ ቆቃ፣ ዝዋይ፣ አባያና ጫሞ ሓይቆች ላይ የእምቦጭ አረም ተከስቷል። 

የእምቦጭ አረሙ ሊከሰት የቻለው በውሃ ብክለት፣ በተፋሰስ መራቆት፣ ከመጠን ባለፈ የተፋሰስ ውሃ አጠቃቀምና ዓሳ ማስገር ጋር በተያያዘ መሆኑን አመላክተዋል።

በተለይ በተፋሰሶች ዙሪያ የእርሻ ልማት መስፋፋት፣ የውኃ አካላት ላይ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች፣ ከከተማና ከኢንዱስትሪ፣ ከእርሻ ማሳ ወደ ሀይቆች የሚገቡ ፍሳሾችና ጎርፍ አረሙ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውቀዋል። 

በመሆኑም ይህንን ችግር ለመከላከልና አረሙን ለማስወገድ የሚያስችል የእምቦጭ መከላከል ብሄራዊ ስትራቴጂ ተነድፎ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ለእምቦጭ ማስፋፋት ምክንያት የሆነውን ችግር ለመቅረፍ ይሰራል ብለዋል። 

አረሙን በሰው ሀይልና በማሽን ከማስወገድ ባለፈ እንዴት እምቦጭን በዘላቂነት መከላከል እንደሚቻል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

በውሃ አካላት ዳር የሚካሄዱ የእርሻ ልማቶችን በሰርቶ ማሳያዎች ወደ ተቀናጀ ‘የአሳ ፓንድ’ ልማት ለመቀየር አርሶ አደሮችን በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ተሞክሮ ለማስፋፋት ትኩረት መሰጡትን አስታውቀዋል። 

የውሃ አካላትን በዘላቂነት ከብክለትና ከአረሙ መስፋፋት ለመከላከል በተለያዩ ዘዴዎች ከእርሻ ስነ-ምህዳር በጎርፍ ምክንያት ታጥበው የሚመወጡትን ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ በቦታዎቹ ላይ ለማስቀረት ግብ ተይዞ እየተተገበረ መሆኑን አውሰተዋል። 

እንደ አቶ ዮሐንስ ማብራሪያ የተለያዩ አገሮችን ተሞክሮች በማየት እምቦጭ አረምን ለኃይል አማራጭነትና ለሌላ ተግባር ለመጠቀም እቅድ እንዳለ ስትራቴጂው የሚያሳይ ሲሆን በዘንድሮም ዓመት በሚካሄደው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እንቅስቃሴ የእምቦጭ አረምን ለመከላከል አንድ አካል ተደርጎ ርብርብ ይደረጋል። 

በመድረኩ ላይ የእምቦጭ ዓረም አመጣጥ እና የአወጋገድ ሥርዓት ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ‘ኢንቫይሮመንታል ቶክስኮሎጂ’ የ3ኛ ድግሪ ተማሪ ዳንኤል ወልደሚካኤል በሰጡት አስተያየት የእምቦጭ አስከፊው ገጽታ በአጭር ጊዜ ሰፊ የውሃ አካላትን መውረሩ ነው። 

በተለይ የውሃ አካላትን በፍጥነት በመውረር ኦክስጂንና የፀሐይ ብርሃን እንዳይገባ በማድረግ ውሃ ውስጥ ያለውን ህይወት በሙሉ እንዳይቀጥል ያደርገዋል ብለዋል በመሆኑም እምቦጭ አረም በብዝሃ ሕይወት አንዲሁም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ የደቀነው ሥጋት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። 

አረሙ አንዴ ዘሩን ውሃ ውስጥ ካፈራ ለ20 ዓመት የመቆየት አቅም እንዳለው ጠቅሰው አረሙን በተለያዩ ዘዴዎች ለመከላከል እየተደረገ ያለው ርብርብ ጥሩ ቢሆንም በቂ አይደለም ብለዋል። 

አረሙ ከሚያደርሰው ጉዳት አንፃር ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የተለያዩ ሳይንሳዊ ጥናቶችን ማካሄድና የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ ወደ ሀገራችን ማምጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የስምጥ ሸለቆ ቤዚን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዴቢሶ ዴዴ በበኩላቸው በስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ውስጥ ጫሞ፣ አባያ፣ዝዋይ ሓይቆች በእንቦጭ አረም ከተወረረ ወዲህ በሐይቆቹ ብዝኃ ህይወት ላይ ከፍተኛ ችግር አስከትሏል።

ጽህፈት ቤቱ ችግሩን ለመፍታትም ከኦሮሚያ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል፣ በዚህም አበረታች ውጤት እየተገኘ መምጣቱን ገልጸው ይህንን ለማስቀጠል እየተሰራ ነው ብለዋል።

እስካሁን አረሙ ያልተከሰተባቸውን ሐይቆች አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻልም በሐይቆቹ ዳርቻ የተለያዩ እጽዋትን ለመትከል ይሰራል ብለዋል።

መድረኩ የተዘጋጀው ባለፈው ዓመት አረሙን ለመከላከል በተደረገው ጥረት በተገኙ ውጤቶችና ባጋጠሙ ተግዳራቶች እንዲሁም በዚህ ዓመት እቅድ ላይ በመምከር ወደ ዘመቻ ለመግባት ታስቦ መሆኑን አስረድተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በቃና በተነደፈው ስትራቴጂክ መሰረት በክልሉ አረሙን ለማስወገድ፣ የውኃና አካባቢ ጥበቃን በዘላቂነት ለማስፋን፣ ነፃ የሓይቅ ዳርቻን ለመፍጠር ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እንዲሁም የተፋሰሱ ውሃ ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎችና ተቋማትን በማሳተፍ በደንበል ሓይቅ በእምቦጭ የተወረረውን 150 ሄክታር አረም ለማስወገድ ካለፈው ዓመት ወዲህ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝና በዚህም ውጤት እየተገኘ መሆኑን አስረድተዋል።

ዘንድሮም ከዝዋይ ሓይቅ ባሻገር በቆቃ አካባቢ በአረሙ የተወረረ 200 ሄክታር የውሃ አካላት በዘመቻ ለማስወገድ መታቀዱን አቶ ተሻለ አስታውቀዋል።

በመድረኩ ላይ ከኦሮሚያ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች የተውጣጡ ባለድረሻ አካላት እና በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ የዩኒቪርሲቲ ምሁራን ተሳትፈዋል።