ሀገር በቀል እውቀቶች ለአገር እድገትና ሰላም አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ማጠናከር ይገባል -ምሁራን

283

ሐረር (ኢዜአ) ጥር 17/2015 ሀገር በቀል እውቀቶች ለአገር እድገትና ሰላም አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ሲሉ ምሁራን ገለጹ።

በኦሮሞ የገዳ ስርዓት፣ ቋንቋ፣ ስነ-ጽሁፍ እና ባህል ላይ ያተኮረው 5ኛው የኦሮሞ ጥናት ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመካሄድ ላይ ነው። 

በሐረማያ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ረታ ዱጉማ እንደገለፁት በማህበረሰቡ ውስጥ በርካታ ማህበራዊ፣ አስተዳደራዊና ሌሎች ነገሮች የሚመሩበት ሀገር በቀል እውቀቶችና ስርዓቶች ይገኛሉ። 

ሀገር በቀል እሴቶቹም ለአብሮ መኖር፣ ለግጭት አፈታት፣ ለልማት፣ ለመከባበርና ለመቻቻል ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል። 

እነዚህን ሀገር በቀል እውቀቶችን በጥናትና ምርምር በማገዝ ለአገር እድገትና ሰላም እንዲሁም ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው። 

በዚህም ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የገዳ ጥናት ተቋም በመመስረት ህብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ፣ ስርዓቶቻቸው በሙሉ ስራ ላይ እንዲውል የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።  

የጅማ ዩኒቨርሰቲ የምርምርና የማህበረሰብ ጉዳዮዎች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ነፃነት ወርቅነህ በበኩላቸው አኩሪ የሆኑ አገር በቀል ባህሎች እና እሴቶችን ለማጎልበት፣ ለሰላምና ለእድገት ለማዋል ምሁራን የሚያካሂዱትን የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማበልፀግ ይገባል ብለዋል። 

ላለፉት ሰባት አመታት የኦሮሞ ጥናት ተቋም በመመስረት የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በማከናወን በአፈ-ታሪክ ብቻ የሚታወቁትን አኩሪ እሴቶችን በመሰነድ፣ በድረ-ገጽ እና በሌሎች መንገዶች ለህዝብ እንዲደርሱ ተደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል። 

ሀገር በቀል እውቀቶችና ባህሎችን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍና ለማቆየት በዘርፉ የሚገኙ ምሁራን የምርምር ሚናቸውን ማጎልበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። 

የምጣኔ ሃብት ባለሞያው ዶክተር ጉቱ ቴሶ በበኩላቸው ሀገር በቀል እውቀቶች ለአገር ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ለማገዝ ያላቸው ሚና የጎላ በመሆኑ ምሁራን በዘርፉ የሚያከናውኑትን የጥናትና ምርምር ስራ ማጎልበት ይገባል ብለዋል። 

''በተለይ በማህብረሰቡ ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ስርዓቶችና እሴቶች ህዝቡ በቀላሉ ይቀበላል'' ያሉት ዶክተር ጉቱ እሴቶቹን በማጎልበት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም በሰላም ግንባታና በሌሎች የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ይገላል ሲሉ ገልጸዋል። 

በኮንፍረንሱ ላይ ከሐረማያ፣ ጅማ፣ ከወለጋና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ምሁራን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ከኦሮሚያ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም