በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በ2010/11 የምርት ዘመን 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል

71
ነቀምቴ መስከረም 24/2011 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በ2010/11 የምርት ዘመን 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ  የአዝርዕት ባለሙያ ወይዘሮ በቀለች ማሞ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዞኑ በ315 ሺህ 223 ሄክታር መሬት ላይ ከተዘራው ሰብል ቡቃያ ምርቱ እንደሚሰበሰብ በቅድመ ምርት ግምገማ ተረጋግጧል። በዚህም በ2009/10 የምርት ዘመን ከተገኘው በ754 ሺህ 890 ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት እንደሚገኝ ተናግረዋል። የዞኑ አርሶ አደሮች በመሥመር በመዝራት፣ማዳበሪያና ምርጥ ዘር የመሳሰሉት ግብዓቶችን በመጠቀማቸውና የዝናብ ስርጭቱ ለምርቱ ጭማሪ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ባለሙያዋ አስረድተዋል። በጉዱሩ ወረዳ የድላሎ ባሮ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፉፋ ቶሌራ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ሶስት ዓመታት በባለሙያዎች ድጋፍ እየታገዙ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው ማሳደጋቸውን ተናግረዋል ። የመኽር አዝመራ በጥሩ ይዞታ ላይ በመሆኑ 15 ኩንታል ጤፍና 80 ኩንታል በቆሎ አገኛለሁ የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል። ቡቃያቸው በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ በቅድመ ምርት ግምገማው ወቅት  በባለሙያዎች እንደተገለጸላቸው የተናገሩት አርሶ አደር ገበየሁ ጭምዴሳ በወቅቱ መሬታቸውን አርሰውና አለስልሰው መዝራታቸውን ገልጸዋል፡፡ ፀረ አረም መድኃኒት በመጠቀም ቡቃያቸውን እንደተንከባከቡ ያስታወቁት አርሶ አደሩ በቅድመ ምርት ግምገማው መሠረት ቢያንስ 70 ኩንታል በቆሎ፣10 ኩንታል ጤፍና ከስድስት ኩንታል በላይ የኑግ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል፡፡ በዞኑ በአብዛኛው በቆሎ፣ስንዴ፣ጤፍ፣ገብስ፣ባቄላና ኑግ የሚመረት ሲሆን በዘንድሮው የመኽር አዝመራ 86 ሺህ 800 አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም