የእንስሳት በተሃዋሲያን መጎዳት የቆዳና ሌጦ የውጭ ንግድ ላይ ተጽዕኖ ማሳረፉ ተገለጸ

59
አዳማ መስከረም  23/2011 በእንስሳት ሃብት ላይ የሚደርሰው የተሃዋሲያን ጉዳት ሃገሪቱ ከቆዳና ሌጦ የውጭ ንግድ ልታገኝ የሚገባትን ጥቅም እያሳጣት እንደሚገኝ ተገለጸ። በኦሮሚያ ክልል በዘርፉ የሚታየውን  የጥራት ጉድለት፣ የግብይትና የአቅርቦት ችግር ላይ ያተኮረ ምክክር በአዳማ ከተማ ተካሒዷል። የኦሮሚያ እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ከፈና ይፋ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በውጪ ጥገኛ ተዋሲያን ምክንያት በእንስሳት ሀብቱ ላይ በሚደርሰው ጉዳት ክልሉም ሆነ ሀገሪቷ ከቆዳና ሌጦ ተገቢውን ጥቅም እያገኘች አይደለም። በክልሉ በዓመት በአማካይ ከ90 ሺህ ቶን በላይ ቆዳና ሌጦ ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ቢኖርም በችግሩ ምክንያት ባለፈው ዓመት የቀረበው ቆዳና ሌጦ 20 ሺህ ቶን ብቻ መሆኑን አስረድተዋል ። በችግሩ ምክንያትም 70 ሺህ ቶን ቆዳና ሌጦ ተበላሽቶ መቅረቱን ሃላፊው አስረድተዋል። ተህዋሲያኑ በቆዳና ሌጦ ምርት ላይ በሚያደርሱት ጉዳት የምርቱን ተፈላጊነት   እንደሚቀንሰው የገለጹት ደግሞ በግብርናና እንስሳት ሀብት ልማት ሚኒስቴር የሰበታ የእንስሳት ላቦራቶሪ ማእከል ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ገብሬ ናቸው። ጉዳቱ ተላላፊ በሽታዎችን ወደ ውስጣዊ የእንስሳት አካል እንዲገቡ በማድረግ የስጋ መበላሸት፣ የወተት ምርትና የእንስሳት ክብደት መቀነስን ጨምሮ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል። የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ሀብቱ በስፋት ከሚገኝበት ቦታ የራቁ መሆናቸው ፣ ህገ-ወጥነትን ለማስወገድ የቅንጅት አሰራር ያለመዘርጋት፣የግንዛቤ እጥረትና ሌሎች ችግሮች በዘርፉ የተለዩ ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸዋል። የኦሮሚያ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ገመችስ መላኩ በበኩላቸው ችግሮችን ለማቃለል ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከልና አምራቹን ከገዥው ጋር እንዳይገናኝ የሚያደርጉትን ደላሎች በመከላከል ህጋዊ ነጋዴዎችን በባለቤትነት በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የአቅርቦትና የግብይት ችግርን ለመፍታት በቆዳና ሌጦ አሰባሰብ፣ አዘገጃጀትና አጠባበቅ ላይ አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩና ሙያተኛው በቂ ክህሎትና ግንዛቤ እንዲያገኝ አቅም የመገንባት ሥራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። በአዳማ ከተማ ትላንት በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆኖዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም