በኢትዮጵያ ሙያዊ ስነ-ምግባርን ያከበረ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት እንዲጎለብት በትኩረት እየተሰራ ነው

229

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2015 በኢትዮጵያ ሙያዊ ስነ-ምግባርን ያከበረ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት እንዲጎለብት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር "የተቀናጀ የጤና ሙያ ሥነ ምግባር ትግበራ ፍትሀዊ ደህንነቱን ለጠበቀና ሁሉን ተደራሽ ለሚያደርግ የጤና አገልግሎት" በሚል መርህ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ መኮንን እንዳሉት፤ የጤና አገልግሎት ከህብረተሰቡ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ከህዝቡ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በመሰብሰብና ምርምራ በማድረግ በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል፡፡

በተለይም ከሁለት ዓመት ወዲህ የቴክኒክ ኮሚቴ በማዋቀር የጤና ባለሙያዎች በህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ወቅት የሚፈፅሙትን የሥነ ምግባር ጉድለት በመመርመር ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች በህክምና ወቅት ተገልጋዩን በቅንነት ከማስተናገድ ጀምሮ የህክምና መመሪያዎችን እስከመስጠት ባለው ሂደት ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን አክብረው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የተገልጋዩን ቅሬታና በጤና ተቋማት የተፈጠረውን ሙያዊ ሥነ ምግባር ግድፈት በመመርመር ከቃል ማስጠንቀቂያ ጀምሮ የሙያ ፈቃዳቸውን እስከማገድ የሚደርስ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህግ ባለሙያ አቶ ዳንኤል ሰሎሞን በበኩላቸው፤ የጤና ባለሙያዎች በህክምና ወቅት በታካሚዎች ላይ በሚያደርሱት አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት በህግ ተጠያቁ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

በመሆኑም የጤና አገልግሎት ሥነ ምግባር ጉድለት የሚፈዕሙ ባለሙያዎች ጉዳያቸው በሥነ ምግባር ደንብ ብሎም በፍታህቤር እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ማንኛውም የህክምና ባለሙያ ተገቢ የህክምና አገልግሎት ባለመስጠትና በከባድ ቸልተኝነት በታካሚው ላይ ጉዳት ካደረሰ በወንጀል ይጠየቃል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም