የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል

145

ጎባ ኢዜአ ጥር 14/2015፦ የድርቅ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ለተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን በባሌ ዞን የሀረና ቡሉቅ ወረዳ አርሶና አርብቶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ ከ95 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ያካለለ የተፋሰስ ልማት ስራ ተጀምሯል።

ከወረዳው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሀሰን ማህሙድ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው በተፈጥሮ ሀብት ላይ እየደረሰ በነበረው ውድመት የምንጮች መድረቅና የአካባቢ መራቆት የተነሳ ለድርቅ ተጋላጭ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለተፈጥሮ ሀብት ልማት እንክብካቤ በተሰጠው ትኩረት ግን ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች እንዲያገግሙ እድል መፍጠሩን ነው የተናገሩት።

አካባቢዎቹ ወደ ልምላሜ ከመላበሳቸው ባለፈ ለቤት እንስሳት ግጦሽ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አብዳ ሶሞ ናቸው።

የድርቅ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ለተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አልይ መሀመድ እንዳሉት በተፋሰስ ልማት ስራው በዞኑ 87 ሺህ ሄክታርን ያካለለ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ይከናወናል።

ለ60 ቀናት በሚቆየው ስራም ከ300 ሺህ በላይ ሕዝብ እንደሚሳተፍ ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተካሄዱት የተፋሰስ ልማት ሥራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ያነሱት ኃላፊው፤ በዘርፉ የሚጠበቀውን ስኬት ለማስመዝገብ እንዲቻል ሕዝቡ በሥራው በንቃት እንዲሳተፍ አስገንዝበዋል።

በልማቱ ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል 50 ሄክታር የተጎዳ መሬት ማካለልና ከ57 ሺህ ሄክታር በላይ የእርከን ሥራዎች ይገኙበታል።

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው በዞኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ የአካባቢን አየር እርጥበት በመቀየር ምርትና ምርታማነት አንዲጎለብት ማስቻሉን ተናግረዋል።

ለሥራው ውጤታማነት ህዝቡ በንቃት ለማሳተፍ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አቶ አብዱልሀኪም አመልክተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ባስተላለፉት መልዕክት በክልሉ በዘንድሮው የበጋ ስራ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ያካለለ የተለያዩ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት መጨመር ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል።

በክልሉ በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቁ የአርብቶ አደር አካባቢዎችን የድርቅ ተጋለጭነት ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሰራም ነው አቶ ጌቱ ያመለከቱት።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ስራ በባሌ ዞንና ቤሎችም የክልሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም