የሚልኪዌይ ጋላክሲ ማሳያ ሞዴል የሆነ የስፔስ ሳይንስ የምርምር ማዕከል በእንጦጦ ኦብዞርቫቶሪ እየተገነባ ነው

245

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 14 ቀን 2015 የመሬት ሶላር ሲስተም የምትገኝበትን የሚልኪዌይ ጋላክሲ ማሳያ ሞዴል የሆነ የስፔስ ሳይንስ የምርምር ማዕከል በእንጦጦ ኦብዞርቫቶሪ እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

 የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት ከ700 ሚሊየን ብር በላይ በመመደብ ይህንና ሌሎች የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየገነባ መሆኑንም ገልጿል።

በፊዚክስ "ሚልኪዌይ ጋላክሲ" እየተባለ የሚጠራው በሶላር ሲስተም ውስጥ መሬት የምትገኝበት ምህዋር ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ መሬት አነስተኛ አካል መሆኗም ይነገራል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት ፕሮጀክቶች አስተባባሪ ኢንጂነር ማህሌት መለሰ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የመሬት ሶላር ሲስተም የምትገኝበትን የሚልኪዌ ጋላክሲ ማሳያ ሞዴል የስፔስ ሳይንስ የምርምር ማዕከል በእንጦጦ ኦብዞርቫቶሪ የስፔስ ሳይንስ የምርምር ማዕከል እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

ለማዕከሉ ግንባታ 287 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ የማእከሉ ግንባታ የምንኖርባት ዓለም ከሚልኪዌይ ምን ያህል አናሳ መሆኑን ለማሳየት ስለመሆኑ አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ በዘርፉ ያሉ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች ጭምር የምንኖርባትን ዓለም ከሚልኪዌይ ጋላክሲ ጋር ለማነጻጸር የሚጠቅም መሆኑንም ኢንጂነር ማህሌት አብራርተዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ጥራትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ከአንድ ወር በኋላ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ብለዋል።

በእንጦጦ ኦብዞርቫቶሪ ማዕከል ከዚህ በተጨማሪ ለስፔስ ሳይንስ ተመራማሪዎችና ለተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ላቦራቶሪዎችና ሙዚየም በመገንባት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

May be an image of outdoors

የእንጦጦ ኦብዞርቫቶሪ ማዕከልን ለተመራማሪዎችና ለጎብኚዎች ጭምር ምቹ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ደረጃውን የጠበቀ የወርክሾፖ ማዕከል ግንባታ በ198 ሚሊዮን ብር እየተከናወነ ሲሆን ግንባታው አሁን ላይ 60 በመቶ መድረሱንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም