በቄለም ወለጋ ዞን ከ40ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በቡና ችግኝ ሊለማ ነው

61
ነቀምቴ ግንቦት 12/2010 በቄለም ወለጋ ዞን ከ40 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የቡና ችግኝ ለመትከል እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የባለስልጣኑ የቡና ልማት ባለሙያ አቶ ገመቹ ሽፈራው እንዳስታወቁት የቡና ችግኝ ተከላ ሥራ የሚከናወነው በዞኑ በሚገኙ 13 ወረዳዎች ውስጥ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የዝግጀት ሥራው እየተከናወነ ነው፡፡ በዞኑ ከግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሚካሄደው ተከላ ከ248 ሚሊዮን102 ሺህ በላይ የቡና ችግኝ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል ፡፡ ችግኙ በመንግስትና በግል የችግኝ ጣቢያዎች መዘጋጀቱን የተናገሩት ባለሙያው፣ ለችግኝ ተከላ ሥራው አስቀድሞ የመትከያ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውንና በእዚህም ከ82 ሺህ በላይ የዞኑ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ገመቹ እንዳሉት፣ በዞኑ በዘንድሮ ዓመት ለተከላ የተዘጋጀው የቡና ችግኝ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ11 ሚሊዮን 686 ሺህ ብልጫ አለው፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አንዳንድ የዞኑ አርሶአደሮች በበኩላቸው ለቡና ችግኝ ተከላው ከወዲሁ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በአንፊሎ ወረዳ የሸበል ፋና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዳግም ራጋ እንዳሉት በግላቸው 18 ሺህ የቡና ችግኞችን አዘጋጅተው ለመትከል በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአንድ ሄክታር ከሩብ መሬት ላይ 3 ሺህ ጉድጓዶችን ቆፍረው ማዘጋጀታቸውን የተናገሩት አርሶአደሩ፣ ከሚተክሉት የቡና ችግኝ በተጨማሪ 15ሺህ የቡና ችግኞችን ለአካባቢው አርሶ አደሮች ለመሸጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ በሦስት ሄክታር መሬት ላይ 14 ሺህ የቡና ችግኞችን በማዘጋጀት ለተከላ ጉድጓድ ማዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የአሺ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቀነኒ ረጋሳ ናቸው ። አርሶ አደሩ ካዘጋጁት መሬት የሚተርፈውን 4 ሺህ የቡና ችግኝ በ2ሺህ 400 ብር በመሸጥ ገቢያቸውን ለማሳደግ ማቀዳቸውንም አመልክተዋል፡፡ በሐዋ ገላን ወረዳ የሐዋ አፍንጮ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታምሩ ያደታ በበኩላቸው 24ሺህ የቡና ችግኝ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ ካላቸው የቦታ ጥበት የተነሳ አብዛኛውን ችግኝ ለሽያጭ እንደሚያቀርቡ የገለጹት አርሶአደር ታምሩ፣ በግል ለሚተክሉት ጉድጓድ አዘጋጅተው የተከላውን ጊዜ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል። በቄለም ወለጋ ዞን 362 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በቡና ልማት መሸፈኑን የዞኑ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን መረጃ ያሳያል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም