የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱላቸው በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ

95
ጋምቤላ መስከረም 23/2011 የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች እንዲፈቱላቸው የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች/ዳልዲም/ ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ። በወጣቶቹ ለተነሱ ጥያቄዎች የክልሉ መንግሥትና መሪው ድርጅቱ በተቻለ ፍጥነት ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት ገለጹ። መነሻቸውን በጋምቤላ ከተማ መስተዳድር ያደረጉት ወጣቶቹ  የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት ነበር መድርሻቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ያደረጉት። በጽህፈት ቤት ሲደርሱም ወጣቶች ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግጫቸውን አሰምተዋል ። ሰልፈኞቹ ባሰሟቸው የአቋም መግለጫ እንዳመለከቱት ጥማታቸው የስልጣን ሳይሆን፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን አመልክተዋል ። በክልሉ ተንስራፍቶ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈታ የአመራር ለውጥ እንደሚያስፈልግና ለለውጡ ስኬትም የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ  እንዲታከልበት ጠይቀዋል። በክልሉም ሆነ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥና የሰላም ጉዞ  ለማደናቀፍ የሚታገሉ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በጽናት እንደሚታገሏቸውም ገልጸዋል። ወጣቶቹ መስከረም 13 እና 14 ቀን 2011 በወጣቶች ላይ ግድያ የፈጸመው አካል ጉዳይ ተጣርቶ በአስቸኳይ ለህግ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል። ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል ወጣት ኡሞድ ኡቻላ እንደተናገረው በከተማው ብሎም በክልሉ የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮች ተሰራፍተው ይገኛሉ። በመሆኑም ለክልሉ ልማትና የመልካም አስተደዳር ችግሮች የሚፈቱና ሀገራዊ ለውጡን ወደፊት የሚያራምድ አመራር ያስፈልጋል ብሏል።  ሰልፉን ማድረግ ያስፈለገው በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ በክልሉ እንዲተገበርና የለውጡ አራማጅ አመራሮች እንዲመጡ በማለም ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የሰልፉ አስተባበሪ ዶክተር ማኝ ኡቻላ ናቸው።  ወጣት አንድነት አረጋ በሰጠው አስተያየት እንደተናገረው በሰልፉ የተካፈለው በክልሉ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች ሥራ እንዲፈጠርላቸው ለማሳሰብ ነው ። በክልሉ የተወሰኑ የስራ እድሎች ቢፈጠሩም፤ ወጣቶች ሳይሆኑ ባለሀብቶች እንደተጠቀሙበት የገለጸው ወጣቱ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት በትኩረት መስራት እንዳለበት ተናግሯል።ከጎሰኝነትና ከዘረኝነት የፀዳና በአገራዊ ለውጥ የሚያምን አመራር እንደሚያስፈልግ የገለጹት ደግሞ ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ ወጣት ጆን ኡጁሉ ነው፡፡  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት በወጣቶች የተነሱ ጥያቄዎችን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ወጣቶቹ ያቀረቧቸው የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች አግባብነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ወጣቶቹ የአመራር ለውጥ ያስፈልጋል ብለው ያነሱት ጥያቄም ተገቢ መሆኑንና ለውጡ ግን በድርጅቱ ደንብና የአሰራር ሂደት እንደሚሆን መዘንጋት የለበትም ብለዋል። ወጣቶች አሉ ያሏቸውን ችግሮች በሰላማዊ ሰልፍ ማቅረባቸው የሰለጠነና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን በማድነቅ የተነሱትን ጥያቄች የክልሉ መንግሥት ከመሪ ድርጅቱ ጋር በመሆን በተፋጠነ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም