በቻን ውድድር ለመቆየት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሊቢያ አቻው ጋር ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል

207

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 13/2015 ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከሊቢያ ጋር ዛሬ ወሳኝ ፍልሚያ ታደርጋለች።

የዋልያዎቹ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋ በዛሬው ጨዋታ ሊቢያን በማሸነፍ እና በሞዛምቢክ መሸነፍ ላይ የተመሰረተ ነው።

በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ሰባተኛው የቻን ውድድር ዛሬ ዘጠነኛ ቀኑን ይዟል።

በምድብ አንድ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በ ‘19 May 1956’ ስታዲየም ኢትዮጵያ ከሊቢያ ከምሽቱ 4 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና አማካዩ ጋቶች ፓኖም ጨዋታውን አስመልክቶ ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

"በሁለቱ የምድብ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደችው ሊቢያ ጠንካራ ናት፤ ይህንን የመጨረሻ ጨዋታ ለማሸነፍ የሚቻለንን እናደርጋለን" ብሏል አሰልጣኝ ውበቱ።

እኛ ካሸነፍን የአልጄሪያ እና ሞዛምቢክ የምድብ ጨዋታ መጠበቅ ይኖርብናል ያለው አሰልጣኙ በተቃራኒው ሊቢያ ነጥብ ይዘው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ብሎ እንደሚጠብቅ ገልጿል።

አሰልጣኝ ውበቱ በሁለቱ ጨዋታዎች ያባከኗቸውን የግብ ዕድሎችን በማንሳት የተገኙ እድሎችን ወደ ግብ መቀየር የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ ወሳኝ መሆኑን አመልክቷል።

"አናባ ያለው ቀዝቃዛ የአየር ንብረትም ከአልጀርስ ለወጥ ያለ መሆኑ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል" ሲል ገልጿል።

የአማካይ ተጫዋቹ ጋቶች ፓኖም በበኩሉ "የዛሬው ጨዋታ ከባድ እንደሚሆን እናውቃለን።

የማለፍ ዕድላችን በሌላ ቡድን ላይ ቢመሰረትም ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የተቻለንን ሁሉ በሜዳ ላይ እናደርጋለን" ብሏል።

"ውድድሩ ፈታኝ ነው ሁሉም ተጫዋች በዚህ ውድድር ራሱን በማሳየት በትላልቅ ሊጎች ላይ የመጫወት ሕልም አለው፤ እኔም ጠንክሬ በመስራት ራሴን ማሳየት እፈልጋለው" ሲል ጋቶች ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድቡ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ያገኘው አንድ ነጥብ ብቻ ነው።

በአልጄሪያ 1 ለ 0 ሲሸነፍ ከሞዛምቢክ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይቷል።

ዋልያዎቹ ወደ ጥሎ ማለፉ ለመግባት በዛሬው ጨዋታ ሊቢያን ሁለት እና ከዛ በላይ የግብ ልዩነት በአሸነፍ የሞዛምቢክ በአልጄሪያ መሸነፍን ይጠብቃል።

የኢትዮጵያ ተጋጣሚ ሊቢያ በምድብ አንድ ባደረገው ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፎ ከምድቡ ወድቋል።

ዋልያዎቹ በሚገኙበት ምድብ አንድ አስተናጋጇ አገር አልጄሪያ በኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ከምሽቱ 4 ሰአት ከሞዛምቢክ ጋር ትጫወታለች።

አልጄሪያ በምድቧ ያደረገችውን ሁለት ጨዋታ አሸንፋ ወደ ቀጣዩ ዙር ቀድማ ማለፏን አረጋግጣለች።

ሞዛምቢክ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።

ትናንት በቻን ውድድር በምድብ አራት አንጎላ ከሞሪታኒያ እንዲሁም በምድብ አምስት ኮንጎ ብራዛቪል ከኒጀር ያደረጉት ጨዋታ በተመሳሳይ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የቻን ውድድር እስከ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም