የከተራ እና ጥምቀት በዓላት በሰላም ተጠናቅቀዋል-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

208

ጥር 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) የከተራ እና ጥምቀት በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመግለጫው ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

በዓላቱ በድምቀት እና በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት ሁሉ መንግሥት ምስጋና ያቀርባል።

በዓላቱ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ገጽታቸውን ጠብቀው የሕዝብ አብሮነትን አጉልተው፤ ኢትዮጵያውያንን ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ቦታ ስበው፣ ብዙ ሚሊዮን ቱሪስቶችን አስተናግደው በስኬት ተጠናቅቀዋል።

በዚህም በመላው ኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ ታቦታት ወደ መንበሮቻቸው ተመልሰዋል። ላለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነት ድባብ ውስጥ የቆዩ አካባቢዎች ሳይቀሩ የዘንድሮን የጥምቀት በዓል በደማቁ አክብረውታል፡ በዓላቱ በመተሳሰብ፤ በአንድነት እና በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ኢትዮጵያዊ እሴትን አድምቀው በሰላም ተጠናቅቀዋል።

በመላው ኢትዮጵያ ሚሊዮኖች በዓሉን ሲያከብሩ የፌዴራል እና የክልል የጸጥታ ኃይሎች ደግሞ ለ24 ሰዓታት ያለመታከት የሕዝቡን ሰላም ጠብቀዋል።

በአንድ አንድ ቦታዎች የጥፋት ተልእኮን ተቀብለው በዓሉን ለማወክ ፍላጎት የነበራቸው የጥፋት ኃይሎች በተቀናጀ የፀጥታ አካላት እና በሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ከሽፏል።

እንደሌላው ጊዜ ሁሉ አሁንም የሰላም ዘብነታቸውን እና የሀገር አለኝታነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል።

በዓላቱን ለመረበሽ ላሰቡ አካላት መፈናፈኛ አሳጥተው ታላቅ ተጋድሎ ፈጽመዋል። የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችም የበዓላቱን ሂደት እየተከታተሉ በማሠራጨት ለበዓሉ በስኬት መጠናቀቅ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

የሃይማኖት አባቶች በዓላቱን አስመልክተው ያስተላለፏቸው መልዕክቶች፤ የሕዝብን አንድነት እና ዘላቂ ሰላማችንን ለማስጠበቅ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።

የተለያዩ የእምነት መሪዎች እና ተከታዮች በዓላቱ በሰላም እና በድምቀት እንዲከበሩ ያሳዩት ተሳትፎ የኢትዮጵያን እውነተኛ መልክ ያሳየ ነው።

ስለሆነም መንግሥት የዘንድሮው የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በሰላም እና በስኬት እንዲጠናቀቁ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናውን ያቀርባል።

ኅብረተሰቡም ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ ላደረገው አስተዋጽዖ መንግሥት ምስጋናውን እያቀረበ፤ በቀጣይ በሚደረጉ ሀገራዊ ክንውኖችም ከመንግሥት ጋር ተባብሮ የኢትዮጵያን ብልጽግና እንዲያሳካ ጥሪውን ያቀርባል።

ጥር 12/2015 ዓ/ም

አዲስ አበባ

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም