አዲስ አበባ ፖሊስ ተጨማሪ አዲስ የደንብ ልብስ ስራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ

266

አዲስ አበባ ጥር 9/2015(ኢዜአ) አዲስ አበባ ፖሊስ ተጨማሪ አዲስ የደንብ ልብስ ስራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ።

የፀጥታ ተቋማትን የደንብ ልብስ እና የደንብ ልብሶቹን አመሳስሎ መጠቀም በህግ የሚያስጠየቅ ተግባር መሆኑ ተገልጿል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የፖሊስ ተቋማትን ለማዘመን በተያዘው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሰረት የፖሊስ ሰራዊት አርማ እና የደንብ ልብስ እንዲቀየር መደረጉ ይታወቃል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ስትራቴጂክ ዕቅዱን መሰረት በማድረግ ልዩ ልዩ አዳዲስ የደንብ ልብሶችን አስመርቆ እየተገለገለ ይገኛል፡፡

ተቋሙ ከዚህ ቀደም ለተወርዋሪ ኃይል ሲጠቀምበት ከነበረው የደንብ ልብስ በተጨማሪ ከጥር 10 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ ተጨማሪ የደንብ ልብስ ስራ ላይ እንደሚያውል በአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ የተወርዋሪ ኃይል እየተገለገለበት ካለው የደንብ ልብስ በተጨማሪነት ስራ ላይ እንዲውል ያደረገው የደንብ ልብስ በተሻለ መልኩ ጥራቱን ጠብቆ የተዘጋጀ መሆኑን ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ገልፀዋል።

ህብረተሰቡን እና ባለድርሻ አካለት ይህንን የደንብ ልብስ የለበሱ የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮችና አባላት መሆናቸውን ተገንዝበው ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ መገልገልም ሆነ አስመስሎ መጠቀም የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን ኃላፊው አስታውሰው የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ የሚገለገሉም ሆኑ አመሳስለው የሚጠቀሙ አካላት ከህገወጥ ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገበ የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ም/ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም