የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና አዋሽ ባንክ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ

244

አዲስ አበባ ጥር 09 ቀን 2015 (ኢዜአ) በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና አዋሽ ባንክ ተፈራረሙ።

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸናና የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፀሐይ ሽፋራው ፈርመውታል።

በሥምምነቱ፤ የባንኩ ደንበኞች የቻትቦትቴክኖሎጂ ወይም (መጻፍ ሳያስፈልግ በንግግር አገልግሎት ባሉበት ቦታ ሆነው የሚያገኙበት) ሥርዓት መዘርጋት ይገኝበታል ተብሏል።

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ወርቁ ጋቸና በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ዘርፎችን ለማዘመን የሚያስችል ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል።

በተለይም የፋይናስ ሥርዓትን ለማዘመን የሚያስችል አዳዲስና ዘመናዊ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥርዓቶችን በተለያዩ ተቋማት የማስተዋወቅና የመዘርጋት ሥራ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የአገሪቱን የምጣኔ ሃብት እድገት ለማስቀጠል የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ ተቋሙ በዛሬው ዕለት ከአዋሽ ባንክ ጋር የደረሰው ሥምምነትም በደንበኞች መረጃ ላይ የተመሰረተ በቴክኖሎጂ የታገዙ የባንክ አግልግሎቶችን ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል።

ሥምምነቱ፤ በባንክ ሴክተር ያሉ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በጋራ ለማበልጸግና የባንኩ ሠራተኞች በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ልምድ ለመለዋወጥ እንደሚያስችልም ነው ያስረዱት።

የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፀሐይ ሽፋራው በበኩላቸው፤ ሥምምነቱ ባንኩ የአገልግሎት አሠጣጡን በቴክኖሎጂ በመደገፍ አሠራሩን ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ ያስችለዋል።

የተደረገው ሥምምነት የባንኩን የአገልግሎት ተደራሽነትና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያጠናክረውም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም የአዋሽ ባንክ የዲጀታል የባንክ ሥርዓትን ለማስፋፋት የያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያግዘው መሆኑንም አንስተዋል።

ስምምነቱ ባንኩ የሚያቀርበውን የብድር አቅርቦት አገልግሎት ለማስፋት እንደሚያስችለውም ጠቅሰዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከአዋሽ ባንክ ጋር በመሆን የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ የባንኪንግ አፕልኬሽን ዘርፍ ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ የባንኩን አገልግሎት ለማዘመን የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን በጋራ እንደሚሠሩም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም