በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን የበለጠ ለማስተዋወቅ እንሰራለን - አምባሳደሮች

207

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 8/2015 በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን የበለጠ ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ አገራት የሚሰሩ አምባሳደሮች ተናገሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚሲዮን መሪዎችና የተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አንድ አካል የሆነውን የጎርጎራ የልማት ፕሮጀክትን የሥራ ክንውንና በጎንደር ከተማ የሚገኘውን የፋሲል ቤተ-መንግሥትን ጎብኝተዋል። 

አምባሳደሮቹ ከጉብኝቱ በኋላ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ኃብት በማልማት ከቱሪዝም ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላል ብለዋል። 

May be an image of 6 people, people standing, monument and outdoors

እነዚህን ፕሮጀክቶችና በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች የቱሪስቶች መዳረሻዎችን የውጭ አገራት ጎብኚዎች መጥተው እንዲጎበኙ የማድረግ ሥራ እንደሚሰሩ አምባሳደሮቹ ተናግረዋል። 

በቱርክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አደም መሃመድ፤ የጎርጎራ የልማት ፕሮጀክት ተፈጥሮን ጠብቆ እየተሰራ ያለ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራ ነው ብለዋል። 

በሌሎች ሀገራት አይተን የምንደነቅባቸውን ነገሮች በሀገር ውስጥ መሥራት የተቻለበትና ይህን የተሰራውን የቱሪስት መስህብ በማስተዋወቅ ረገድ የሁሉም ኃላፊነት ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በካናዳ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፍፁም አረጋ በበኩላቸው፤ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋ በማውጣትና ገጽታዋን በመገንባት አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል። 

እነዚህ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ገቢ ማምጣት የሚያስችሉ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች በመሆናቸው ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተናግረው ከዚህ አንፃር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በዙምባብዌ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ረሺድ መሃመድ፤ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ከእይታ ተደብቀው የነበሩ ኃብቶችን በማልማት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ምቹ የሆነች ሀገር መሆኗን ለማስተዋወቅም ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር፤ የሚሲዮኖች ትልቁ ሥራ የኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲ በመሆኑ ሀገሪቱ የያዘችውን የልማት ሥራ በማስተዋወቅ ገቢ ማስገኘት ይጠበቅብናል ብለዋል። 

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም መዳረሻዎች የበለጠ ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ የቀጣይ ዘመን የኢትዮጵያ የቱሪስት መስህብ ሁነኛ መዳረሻ ይሆናል ብለዋል።

 የጎርጎራ ፕሮጀክት አፈጻጸም ያለበት ደረጃ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በታሰበላቸው ጊዜ መጨረስ እንደሚቻል የሚያረጋግጥ ተምሳሌታዊ የልማት ሥራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

 በመሆኑም ፕሮጀክቱን የጎበኙ አምባሳደሮች በቀጣይ ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም መዳረሻዎች የማስተዋወቅ ትልቅ ሃላፊነት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም