አምባሳደር ሽፈራው ከሱዳን ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

53
አዲስ አበባ መስከረም 23/2011 በሱዳን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለ-ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ አዲስ ከተሾሙት የሱዳን ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ኢንጂነር ከድር ሞሐመድ ጋር ተወያዩ። ኢትዮጵያ እና ሱዳን የሚጋሩትን የውሃ ሃብት አስመልክቶ ይበልጥ በጋራ መስራት በሚችሉበት ሁኔታ እንዲሁም በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። የሁለቱ አገራት ግንኙነት በርካታ ዓመታት ማስቆጠሩን የገለጹት አምባሳደሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስራት ተገቢ ነው ብለዋል። አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ በሱዳን የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጂን ማይክል ዱሞንድ ጋር መወያየታቸውም ተገልጿል። ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በተለያዩ መስኮች በጋራ እንደምትሰራ ጠቅሰው፤ በአገሪቱ እየታየ ያለው ለውጥና እድገት ለሌሎች ጎረቤት አገራት ምሳሌ መሆኑን አምባሳደር ጂን ገልጸዋል። በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙትን የሱዳን አምባሳደር ኤልሳዲቅ ባክሄት አልፋቂ አብደላ የሹመት ደብዳቤ ተቀብለው በሁለቱ አገራት ግንኙነት ዙሪያ አነጋግረዋቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም