በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ ወንጀል በሚፈፀምባቸው ቦታዎች በተደረገ ክትትል ከ280 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

191

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 7/2015 የአዲስ አበባ ፖሊስ የከተማዋን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

በከተማዋ በተደጋጋሚ ወንጀሎችን በሚፈፅሙ ግለሰቦች እና ወንጀል በሚፈፀምባቸው ቦታዎች ላይ በተከናወነ ስራ ከ280 በላይ ተጠርጣሪዎች ከነ ኤግዚቢቶቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ተልዕኮውን በላቀ ደረጃ ለመፈፀም የተለያዩ ዕቅዶችን አቅዶ ወደ ተግባር በመግባት በከተማዋ በተደጋጋሚ ወንጀሎችን በሚፈፅሙ ግለሰቦች እና ወንጀል በሚፈፀምባቸው ቦታዎች ላይ ክትትል ስራ ማከናወኑን ገልጿል።

በዚህም የሌብነት፣ የስርቆት እና ሌሎች ደረቅ ወንጀሎችን ሲፈፅሙ የነበሩ እንዲሁም በተፈፀሙት ወንጀሎች መነሻነት ብቻ ሳይሆን ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችን አስቀድሞ በመለየት እና በፈፃሚዎች ላይ ጥናት አድርጎ የወንጀል እንቅስቃሴያቸውን ለመግታት በተከናወኑ ተግባራት ከ280 በላይ ተጠርጣሪዎች ከነ ኤግዚቢቶቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የልዩ ልዩና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር አለማየሁ አያልቄ ናቸው።

ወንጀል ይፈፀምባቸዋል ተብለው ጥቆማ ከቀረበባቸው ቦታዎች መካከል የየካ እና የቦሌ ክፍለ ከተሞች የሚዋሰኑበት የመገናኛ አካባቢ አንዱ ሲሆን ለተለያዩ የከተማዋ ስፍራዎች የትራንስፖርት መነሻ እና መድረሻ ከመሆኑም በተጨማሪ ህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግዶች በስፋት የሚካሄዱበት እንደመሆኑ የሰው እና የተሽከርካሪ እንቅስቃሴው ቁጥር ከሌሎች አካባቢዎች አንፃር ከፍተኛ ነው።

ይህንን ምቹ ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወንጀል ፈፃሚዎች የኪስ ስርቆት እና ማታለልን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎችን ይፈፅማሉ።

እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከልና ወንጀል ፈፃሚዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ የክፍለ ከተሞቹ ፖሊስ መምሪያ የስራ ሃላፊዎች ተናግረዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል እና የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ም/ዳይሬክተር ኮማንደር ያሲን ሁሴን እና የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል እና የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ም/ዳይሬክተር ኮማንደር ሲሳይ ጣሰው እንደገለፁት፤ በተለይም ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በቅንጅት የመስራቱ ተግባር ተጠናክሮ በመቀጠሉ በርካታ ወንጀል ፈፃሚዎችን ከነኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ መገናኛ ዙሪያ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 15 ተጠርጣሪዎች የተያዙ ሲሆን፤ ከ113 ሺህ ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው ሞባይል ስልኮችም በኤግዚቢትነት ተይዘዋል።

በተመሳሳይ በየካ ክፍለ ከተማ መገናኛ ዙሪያ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 50 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 35ቱ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ናቸው።

200 ሞባይል ስልኮችም በተለያዩ ጊዜያት ተይዘው አብዛኞቹ ለባለቤቶቹ ተመልሰዋል።

በመገናኛ አካባቢ አግኝተን ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ ቀደም ሲል በአካባቢው ላይ ወንጀል ፈፃሚዎች ይበዙ እንደነበር ገልፀው የፖሊስ አባላት በቦታው ላይ በግልፅ እና በስውር የወንጀል መከላከል ስራቸውን ማከናወን ከጀመሩ ወዲህ ቀደም ሲል ከነበረው አንፃር ለውጥ እየታየ መምጣቱን ተናግረዋል።

በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መከላከል እንዲቻል ህብረተሰቡ የሚሰጠውን ጥቆማ እና መረጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም