የተወሰነላቸው የደመወዝ ማሻሻያ ክፍያ እንዳላገኙ የሰመራ ሎግያ ከተማ መምህራን ገለፁ

84
ሰመራ ግንቦት 12/2010 የደረጃ አድገትን ጨምሮ የደመወዝ ማሻሻያ ክፍያ በወቅቱ ባለማግኘታቸው በኑሯቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በአፋር ክልል የሰመራ ሎግያ ከተማ መምህራን ገለጹ፡፡ ከፍያውን በያዝነው ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ለመክፈል አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ በሰመራ ከተማ የሚግሌኪቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ወይዘሮ ሶፍያ መሀመድ እንደገለፁት በሃምሌ ወር 2009 ማግኘት የሚገባቸው የእርከን ጭማሪ እስካሁን አላገኙም፡፡ ለሚመለከተው አካል ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ ባለማግኘታቸው እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት መቋቋም እያቃታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡በሎግያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር መሃመድ ሳልህ በበኩላቸው ባለፈው አመት የትምህርት ደረጃቸውን በማሻሻል ባገኙት ዲግሪ ሊከፈለው የሚገባው ደመወዝ ከዚህ አመት ጀምሮ እንደሚያገኙ የሚገልጽ ደብዳቤ ቢደርሳቸውም እስካሁን የሚከፈላቸው ቀደም ሲል በነበረው የሰርተፊኬት የትምህርት ደረጃ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተደጋጋሚ ለከተማ አስተዳደሩ ችግሩ እንዲፈታላቸው ቢጠይቁም ምላሸ በማጣታቸው ከፍተኛ የሞራል ውድቀት እያደረሰባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የሎግያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር መሃመድ ሀሰን እንደገለፁት  ጥቅምት ወር ማግኘት የነበረባቸው የእርከን ጭማሪ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት እስካሁን ስላልተከፈላቸው እየጨመረ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም እየተቸገሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ስራቸውን በሙሉ ልብና አቅም ትኩረት ሰጥተው ለመስራት ችግር  እየፈጠረባቸው ነው፡፡ የሰመራ-ሎግያ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሃሰን የመምህራን ክፍያ እስካሁን የዘገየው ጽህፈት ቤቱ ባጋጠመው የበጀት እጥረት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ያጋጠመውን የበጀት ችግር በመፍታት እስከ ተያዘው ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ክፍውን ለመፈጸም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይ ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም ጽህፈት ቤቱ የመምህራን ጥቅማ ጥቅምን ለማስከበርና ክፍያውን በወቅቱ ለመተግበር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም