ደኢህዴን የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ገለጸ

83
ሀዋሳ መስከረም 22/2011 በህዝቦች ሁለንተናዊ ተሳትፎና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት/ደኢህዴን የመሪነት ሚናውን አጠናክሮ ለማስቀጠል የጋራ መግባባት ላይ መድረሱን አስታወቀ። 10ኛው የደኢህዴን ድርጅታዊ ጉባኤ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። ጉባኤው ሲጠናቀቅ ባወጣው የአቋም መግለጫ እንደተገለጸው ክልሉን ለአደጋ የዳረጉ ድክመቶችን በጊዜ የለንም መንፈስ የህዝቡን መሰረታዊ የሆኑ የአደረጃጀት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት በቁርጠኝነት ይሰራል፡፡ ደኢህዴን በሀገራችን ፖለቲካዊ ስነ ምህዳሩ እንዲሰፋ ዜጎች የመሰላቸውን ሀሳብ በነጻነት የሚያራምዱበት ዲሞክራሲያዊ አሰራሮችን በመዘርጋት ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው የበኩሉን ድርሻ ይወጣል፡፡ በድርጅቱ አመራርና አባል ዘንድ በአገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴዎችና የደኢህዴን ሚና ዙሪያ ያሉ ብዥታዎችና ውዥንብሮችን በማጥራት ለለውጡ የሚተጋ አባልና አመራር ለማፍራት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ በአቋም መግለጫው አስታውቋል። የለውጥ ሽግግር ላይ የማህበረሰቡ ውስጥ የስርዓት አልበኝነትና ህገ-ወጥነት አዝማሚያ ሊያጋጥም ቢችልም የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ አሉታዊ አዝማሚያዎችን ለመግራት እንደሚሰራም አመልክቷል። ጠንካራ ፖለቲካዊና ርዕዮተ አለማዊ ገጽታን ማጎናጸፍ የሚያስችሉ ብሎም ወቅቱ የሚጠይቀውን ፈጣንና ቀልጣፋ ምላሽ የመስጠት ቁመና ላይ የሚያደርሱ ድርጅታዊ የለውጥ ተግባራትን ማከናወን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በአቋም መግለጫው ተወስቷል፡፡ ጉባኤው በአጠቃላይ በነበረው የአምስት ቀናት ቆይታ በደኢህዴን 9ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ሪፖርትና ቀጣይ አቅጣጫ ዙሪያ በመወያየት የማዕከላዊ ኮሚቴ የድርጅቱንና የኢህአዴግን ስራ አስፈጻሚ አባላት በመመረጥና የኦዲት ኮሚሽን በመሰየም ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም