ለአማራ ክልል ህዝብ ተጠቃሚነት በትኩረት እንሰራለን...የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት

112
ባህርዳር መስከረም 22/2011 ለአማራ ክልል ህዝብ መብት መጠበቅና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በመስራት አለኝታነታቸውን በተግባር ለማረጋገጥ መዘጋጀታቸውን አዳዲስ አዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ገለፁ። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ የሻምበል ከበደ እንደገለፁት የአማራ ክልል ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን እንጂ የተለየ ነገር እንዲደረግለት አይፈልግም። ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥም የማዕካለዊ ኮሚቴው ከሌሎች የኢህዴግ እህትና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ሳይታክቱ መስራት የግድ እንደሚል አስታውቀዋል። "የአዴፓ ጉባኤ በክልሉ የሚስተዋሉ ችግሮች በግልፅ የቀረቡበት ታሪካዊ ጉባኤ ነው" ያሉት አቶ የሻምበል የአማራ ህዝብ ባለፉት ዓመታት በመሰረተ ልማትም ሆነ በሌሎች ተጠቃሚ አንዳልነበር አመልክተዋል። በመሆኑም ይህ ኢ-ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና የልማት ተጠቃሚነት እንዲስተካከልና እኩልነት የሰፈነበት፣ ተጠያቂነት ያለበትና ግልፅነት የተሞላበት አሰራር እንዲዘረጋ የበኩላቸውን እንደሚሰሩ ገልፀዋል። "ቀደም ሲል ይህ ድርጅት በአድርባይነትና በፍርሃት የተሞላና ጥቂቶቹ የሚሉትን ብዙዎቹ አዳምጠው የሚወስኑበት፣ የአማራ ህዝብ ጥያቄ የማይንፀባረቅበትና የህዝብ ድርጅት ነበረ" ያሉት ደግሞ ብርጋዲየር ጀኔራል አሳምነው ፅጌ ናቸው። "አሁን እየተስተዋለ ያለው ፍፁም ለውጥ ነው፤ በዚህም የአማራን ህዝብ እንደ ህዝብ የሚያቆም ጥያቄና አጀንዳ ሆኖ የሚመከርበት ድምጹ የማይታፈንበት አካሄድ ተፈጥሯል" ብለዋል። በዚህ ወቅት መለያየትና መነጣጠል አያዋጣም ያሉት ብርጋዲያር ጀኔራሉ፤ ከግል ፍላጎት ይልቅ ለህዝብና ለሃገር ፍላጎት ራስን አሳልፎ መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል። ይህ መንግስት የህዝብ መንግስት አንደመሆኑ መጠን በየደረጃው ያለው ቢሮክራሲ እንዲፈታ አመራሩና ህዝቡ በጋራ ተግባብቶ መስራት እንደሚኖርበትም አስረድተዋል። "ከዚህ በኋላ የምኖረው ትርፍ እድሜ ነው" ያሉት ብርጋዲየር ጀኔራል አሳምነው፤ ከሞትና ከዋሻ አውጥቶ ለዚህ መድረክ ላበቃኝ ህዝብ የምችለውንና የሚበጀውን ሁሉ ሳልሰስት አደርጋለሁ" ሲሉም አስታውቀዋል። "12ኛው የአዴፓ ጉባኤ አሳታፊ በዴሞክራሲያዊ አግባብ የተካሄደና የአማራ ህዝብ ችግሮች ያለይሉንታና ድርድር በግልፅ የቀረቡበት ነው" ያሉት ደግሞ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው። "የህዝብ የልማትና የዴሞክራሲ ችግር እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሃገር ሰፊ ክፍተት ያለበት ነው" ያሉት አቶ መላኩ እነዚህና መሰል ችግሮች እንዲፈቱም የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። በዚህ ጉባኤም 33 በመቶ ነባር 67 በመቶ ደግሞ አዳዲስና የተሻሉ አመራሮች ለማዕከላዊ ኮሚቴ በመመረጣቸው የህዝብ ችግሮች በአዲስ መንፈስ ይፈታሉ የሚል እምነት አንዳላቸውም ጠቁመዋል። የአዴፓ ድርጅታዊ ጉባኤም በዛሬው እለት አቶ ደመቀ መኮንንን ሊቀመንበር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም የማዕከላዊ ኮሚቴና የስራ አስፈፃሚ አባላትን በመምራጥ ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም